የንግድ ምዝገባ እና የንግድ ሥራ ፈቃድ አዋጅ መሰረታዊ ነጥቦች

የንግድ ምዝገባ እና የንግድ ፈቃድ አሰጣጥን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በማድረግ የንግድ ሥርዓቱ ለመረጃ አያያዝ አመቺ እንዲሆን፣ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያስችል፣ ለመንግስት፣ ለህብረተሰብ እና የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችልና የንግድ ሥርዓቱ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት በማድረግ የአገሪቱን ራዕይ ለማሳካት እንዲቻል፤ አገሪቱ ዘመናዊ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ሕግ እንዲኖራት ለማስቻል የንግድ ምዝገባ እና የንግድ ሥራ ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 (በአዋጅ ቁጥር 1150/2011 አንደተሻሻለ) እና የዚሁ አዋጅ ማስፈጸሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 392/2009 ወጥቶ በስራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት ማንም ሰው የንግድ ምዝገባ ሳያደረግና የጸና የንግድ ስራ ፈቃድ ሣኖረው በንግድ ስራ ላይ መሰማራት የማይችል መሆኑን ጨምሮ ከንግድ ምዝገባ እና የንግድ ሥራ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ያሉት መብትና ግዴታዎች እንዲሁም የሚያስከትሉት የወንጀል ኃላፊነትን በተመለከተ ያሉት ዋና ዋና ነጥቦች በሚከተለው መልክ ቀርበዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የአዋጁ አንቀጽ 5 በንግድ መዝገብ የመመዝገብ ግዴታን ሲያስቀምጥ፡-
• ማንኛውም ሰው በንግድ መዝገብ ላይ ሳይመዘገብ ማንኛውንም ዓይነት የንግድ ሥራ ፈቃድ ማግኘት የማይችል መሆኑን፣
• ማንኛውም ሰው በንግድ መዝገብ የሚመዘገበው ዋና መስሪያ ቤቱ ባለበት ሥፍራ ላይ መሆኑንና በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ቢሠራም በንግድ መዝገብ የሚመዘገበው አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን፣
• በተለያዩ ሥፍራዎች ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት የሚከፍት ማንኛውም ሰው ሥራ ከመጀመሩ በፊት የመጀመሪያ ምዝገባ በተመዘገበበት ቦታ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱን ማስመዝገብና ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ሥፍራ ላለው መዝጋቢ መሥሪያ ቤት ወዲያዉኑ ማሳወቅ ያለበት መሆኑን፣
• በንግድ ሕግ መሠረት ማንኛውም ሰው በንግድ መዝገብ ሲመዘገብ የድርጅት ስሙ ከሌላ ነጋዴ ጥቅም ጋር የማይጋጭ መሆኑን በማረጋገጥ በንግድ መዝገብ ውስጥ መመዝገብ የሚገባው መሆኑን ያስቀምጣል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ንግድ ስራ ምዝገባ ማመልከቻው የንግድ ሥራው ይጀምራል ተብሎ ከሚታሰብበት ቀን አስቀድሞ መቅረብ ያለበት መሆኑን እና መዝጋቢው መሥሪያ ቤት ለምዝገባ የቀረበው የንግድ ማህበር እና የንግድ እንደራሴ በንግድ መዝገብ ከመግባቱ በፊት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር እንዲሰጠው ግብር አስከፋዩን አካል በመጠየቅ ከግብር አስከፋዩ አካል የሚሰጠውን የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የምዝገባ ማመልከቻ ላቀረበው ነጋዴ ወይም የንግድ እንደራሴ በልዩ የምዝገባ መለያ ቁጥርነት በመጠቀም ምዝገባው እንደሚከናወን በአዋጁ ተመልክቷል፡፡ በአንጻሩ ማንኛዉም የንግድ ማህበር ምዝገባ ለውጥ ወይም ማሻሻያ በሚመለከተው የሰነድ አረጋጋጭ አካል በተረጋገጠ በ60 ቀናት ውስጥ ለመዝጋቢው አካል ቀርቦ መመዝገብ ያለበት መሆኑን እና የጽሁፍ ማረጋገጫ ካልተሰጠ በስተቀር የቀረበው የምዝገባ ለውጥ ወይም ማሻሻያ በንግድ መዝገብ እንደገባ የማይቆጠር መሆኑን አዋጁ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ መሰረት፡-
• ማንኛውም ሰው የፀና የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳይኖረው የንግድ ሥራ መሥራት የማይችል መሆኑን፤ ነገር ግን የፀና የንግድ ሥራ ፈቃድ ያወጣ ሰው ለተመሳሳይ የንግድ ሥራ ለሚከፍተው ቅርንጫፍ ተጨማሪ የንግድ ሥራ ፈቃድ እንዲያወጣ የማይገድድ መሆኑን፣
• የማምረት የንግድ ሥራ ፍቃድ ያለው ነጋዴ ያመረታቸውን ምርቶች ብቻ በሚያመርትበት አድራሻ ወይም በሌላ ባስመዘገበበት አድራሻ በጅምላ ለመሸጥ ተጨማሪ የንግድ ፈቃድ እንዲያወጣ የማይገደድ ቢሆንም ያመረታቸውን ምርቶች በችርቻሮ መነገድ የማይችል መሆኑን፤ ሆኖም በልዩ ሁኔታ በችርቻሮ የሚነግድባቸውን ምርቶች ዓይነት በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ሊወሰን እንደሚችል እንዲሁም፤ ማንኛውም የአስመጪነት የንግድ ፈቃድ ያለው ነጋዴ ያስመጣቸውን ምርቶች ለአስመጪነት የንግድ ፈቃዱን ሲያወጣ ባስመዘገበበት አድራሻ በጅምላ ለመሸጥ ተጨማሪ የንግድ ሥራ ፈቃድ እንዲያወጣ የማይገደድ ቢሆንም ያስመጣቸውን ምርቶች በችርቻሮ መነገድ እንደማይችል በአዋጁ ተመልክቷል፡፡
• በሌላ በኩል የንግድ ሥራ ፈቃዱ የተሰጠበት ወይም የታደሰበት የበጀት ዓመት ካበቃ በኋላ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያልታደሰ የንግድ ሥራ ፈቃድ የፀና እንደማይሆን ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በዚህ መሰረትም እነዚህና ሌሎችን የአዋጁን ድንጋጌዎች መተላለፍ አስተዳደራዊ እና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚስከተል ሲሆን የወንጀል ተጠያቂነቱን ለአብነት ብንወስድ፡-
 የፀና የንግድ ሥራ ፍቃድ ሳይኖረው በንግድ ሥራ ተሰማርቶ የተገኘ ማንኛውም ሰው ወይም በንግድ ሥራ ፈቃዱ እንዲሰራ ከተፈቀደለት የንግድ ሥራ ውጭ ሲሰራ የተገኘ ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ሥራ ሲካሄድባቸው የነበሩ የንግድ ዕቃዎች እና የአገልግሎት መስጫ እና የማምረቻ መሣሪያዎች መወረሳቸው እንደተጠበቁ ሆነው ከብር 150,000 እስከ ብር 300,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከ7 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚቀጣ ስለመሆኑ፣
 ሀሰተኛ የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ወይም የንግድ ሥራ ፈቃድ ወይም የእንደራሴ ልዩ የምስክር ወረቀት ያዘጋጀ ወይም ሲጠቀም የተገኘ ማንኛውም ሰው የንግድ ሥራ ሲያካሂድባቸው የነበሩ የንግድ ዕቃዎች፣ የአገልግሎት መስጫ ወይም የማምረቻ መሣሪያዎች መወረሳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከብር 150,000 እስከ 300,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከ7 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል፤
 የንግድ ሥራ ፈቃዱን እንዲጠቀምበት በሽያጭ፣ በኪራይ፣ በስጦታ ወይም በተመሳሳይ ሁኔታ ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት የተከለከለ ሲሆን ይህንን የተላለፈ ማንኛውም ነጋዴ ከብር 50,000 እስከ ብር 100,000 የገንዘብ መቀጮ እና ከ5 ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚቀጣ ሲሆን አሳልፎ የሰጠው ለውጭ አገር ዜጋ በሆነ ጊዜ ከብር 200,000 እስከ ብር 300,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከ7 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 49 ላይ ተዘርዝሮ እናገኛለን፡፡

ቸር ሰንብቱ
ፌናን ተጊበሉ
መጋቢት 13/2013 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment