የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የዜጎች መብት እና የመንግስት ግዴታ በፌደራል አሰተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ
በፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት መሰረታዊ የሆነ መብት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመንግስት የአሰራር ፍትሀዊነት እና ግልፅነት ጭምር የሚገለፅ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 12 የመንግስት አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት እና ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን ደንግጓል፡፡ በዚህ መነሻነትም የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 የወጣ ሲሆን አዋጁ ለዜጎች የተለያዩ መብቶችን የሚሰጥ እና በመንግስት ላይ ደግሞ ግዴታዎችን የሚጥል ነው፡፡ ይህ አዋጅ የወጣበት ምክንያት ይህን ሕገ መንግሰታዊ መርሆ መሰረት በማድረግ የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉትን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ የእነዚህ ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና መመሪያ አወጣጥ መርሆችንና ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ሥርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትሕን ማስፈን በማስፈለጉ ነው፡፡ በአዋጁ መሰረት ዜጎች አገልግሎት የማግኘት መብት፣ የመሳተፍ መብት፣ ቅሬታ የማቅረብ መብት፣ በፍርድ ቤት ክለሳ የመጠየቅ መብት የሚሉት እና ሌሎች መብቶች አሏቸው፡፡
ምንጭ፡- የፍትህ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጽ
Comments
Be the first to add a comment