🌙 የረመዷን ቀናቶች ላይ ምግብና መጠጥ መሸጥ ይቻላልን?
حكم بيع الطعام والشراب في نهار رمضان لغير معذورالحمد لله، والصلاة والسلام على رسول الله وعلى آله وصحبه أجمعين، أما بعد:
يحرم بيع الطعام والشراب وكذا منحه بلا مقابل في نهار رمضان لغير معذور في ترك صومه، لما في ذلك من تسبب في المعصية، وانتهاك لحرمة الشهر، وقد نص على ذلك فقهاء الشافعية وغيرهم.
ረመዷንን መጾም የኢስላም አንዱ መሰረት ነው፡፡ የመጾም አቅም ያለው፣ ለአካለ መጠን የደረሰ፣ ጉዞ ላይ ያልሆነ፣ አካልና አዕምሮው ጤነኛ የሆነና ጾምን የሚከለክሉ ሁኔታዎች ላይ ያልሆነ ሰው ላይ በሙሉ ረመዷንን መጾም ግዴታ ነው፡፡
የረመዷንን ወር መጾም ግዴታነት የነቢዩ ሙሐመድ ﷺ ተከታዮች ላይ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ይልቅ ከዚህ ቀደም ያለፉ የነቢያት ተከታዮች ላይም ጭምር ግዴታ ነበር፡፡
(يَٰٓأَيُّهَا ٱلَّذِينَ ءَامَنُواْ كُتِبَ عَلَيۡكُمُ ٱلصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى ٱلَّذِينَ مِن قَبۡلِكُمۡ لَعَلَّكُمۡ تَتَّقُونَ 183 ) [البقرة: 183]
“እናንተ አማኞች ሆይ እናንተ ላይ ጾም ግዴታ ተደረገ፤ ልክ እነዚያ ከእናንተ በፊት በነበሩት ላይ ግዴታ እንደተደረገው ሁሉ...” አልበቀረህ፡183፡፡
የተፍሲር ሊቃውንት እንደገለጹት የነቢዩ ዒሳ (ዐለይሂስ_ሰላም) ተከታዮችም ጭምር ይጾሙ የነበረው ረመዷንን ወር ላይ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ነው በተለያዩ ምክንያቶች ወሩ ላይ ቀናትን እየጨመሩ ጾማቸው ይዘቱን ለቆ አሁን ያለበት ሁኔታ ላይ የደረሰው፡፡
ይህን ከጥንት ጀምሮ የተከበረን የጾም ወር በቂና ተቀባይነት ያለው ምክንያት (ኡዝር) ሳይኖር መጾሙን ትቶ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ውስጥ መብላትና መጠጣት ዝሙት ከመስራት፣ አስካሪ መጠጥ ከመጠጣትና ከቁማር የከፋ ወንጀል መሆኑን አል ኢማም አዝዘሀቢ (አልከባኢር) ላይ ገልጸዋል፡፡
ረመዷን ላይ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ምግብ/ሻይ ቤት፣ ካፍቴሪያ ወዘተ ከፍተው መደበኛ ሥራቸውን የሚሰሩ፣ የመንገዶች ዳርና ዳር ላይ የጀበና ቡና/ ሻይና ዳቦ ወዘተ ቀለል ያሉ ምግቦችን የሚሸጡ ሙስሊሞችን እናያለን!! ተመጋቢው ማንም ይሁን ማን ረመዷን ላይ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ይህን ማድረጉ በኢስላም የማይፈቀድ ተግባር መሆኑንና ከዚህ የሚገኘው ገቢም ሐላል እንደማይሆን ማወቅ ይገባል!
አል ኢማም ሸምሱዲን አርረምሊ “ሚንሃጅ አጥጣሊቢን” የተሰኘውን የኢማም አንነወዊይ ታዋቂ የሻፊዒየህ መዝሀብ የፊቅህ ኪታብ ሲተነትኑ “ኒሃየቱል ሙሕታጅ” ላይ የሚከተለውን ብለዋል፥
قال العلامة شمس الدين الرملي: "...وَمِثْلُ ذَلِكَ إطْعَامُ مُسْلِمٍ مُكَلَّفٍ كَافِرًا مُكَلَّفًا فِي نَهَارِ رَمَضَانَ، وَكَذَا بَيْعُهُ طَعَامًا عَلِمَ أَوْ ظَنَّ أَنَّهُ يَأْكُلُهُ نَهَارًا كَمَا أَفْتَى بِهِ الْوَالِدُ - رَحِمَهُ اللَّهُ تَعَالَى -؛ لِأَنَّ كُلًّا مِنْ ذَلِكَ تَسَبُّبٌ فِي الْمَعْصِيَةِ وَإِعَانَةٌ عَلَيْهَا..." نهاية المحتاج: (3/182)
“የሙዚቃ መሳሪያን ለዘፋኝ፣ የሐር ጨርቅን ወንድ ልጅ ሊለብሰው፣ የጦር መሳሪያን ለሽፍታ ወዘተ መሸጥ እንደማይቻለው ሁሉ ሙስሊም የሆነ ሰው አንድን በአላህ የማያምን ሰው (ካፊርን) ረመዷን ላይ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ምግብ ሊያበላና እንዲሁም ቀን ላይ ሊበላው እንደሚችል እያወቀ ወይም እየገመተ ሊሸጥለት አይገባም (መሸጥ አይቻልም!) ... ምክንያቱም ይህን ማድረግ አላህ እንዲታመፅ መንስኤ መሆንና ይህም ላይ ማገዝን ስለሚያስከትል ነው” ኒሃየቱል ሙሕታጅ፡ 3/182፡፡
ያለበቂ ምክንያት የተከበረውን ረመዷን የማይጾምን ማንኛውንም ሰው (ሙስሊምም የሚባል ይሁን ካፊር) የጾም ቀን ላይ በመጋበዝም ይሁን ምግብ በመሸጥ ማብላትና ማጠጣት አላህን ማስቆጣትና እርሱን የሚያምጹ ሰዎችን መተባበር ስለሚሆን ወንጀልና ከሙስሊም የማይጠበቅ ተግባር ነው፡፡
ስለዚህም ቀን ላይ የሆነ ሥራ የሚያሰሩት ያለበቂ ምክንያት የማይጾም ሰራተኛም ይሁን፣ የምግብ እርዳታ ሽቶ ቤት እያንኳኳ የሚጠይቅ አቅመ ደካማም ይሁን ረመዷን ቀን ላይ እንዲበላ መተባበርና ምግብ ማቀበል ወንጀል ነው፡፡
ይበልጥ ወንጀሉ ድርብርብ የሚሆነው ደግሞ የተከበረው ረመዷን ወር ላይ ሥራዬ ብሎ ምግብ/ሻይ ቤት ከፍቶ እንዴትኛውም ወርና ጊዜ ቀን ላይ ምግብ እየሸጡና የመጣውን ሁሉ እየመገቡ መዋል ነውና ሙስሊም ሆይ ከዚህ ነውርና ፍጹም ከሙስሊም ከማይጠበቅ ተግባር ተጠንቀቅ/ቂ!!
ካፊር አልጾምም ካለ ራሱን ችሎ ጌታውን ያምጽ እንጂ ሙስሊም የሆነና የጾምን ግዴታነት የሚያምን ሰው የረመዷንን ክብር የማይጠብቁ ሰዎችን ሊተባበርና ምግብ ሊያቀርብላቸው አይገባም፡፡
ለዚህም ነው በዘመናችን የሚገኙ በርካታ ሊቃውንትና የፈትዋ ተቋማትም ጭምር “ረመዷን ላይ በቀኑ ክፍል ጊዜ ውስጥ ምግብ ቤቶችን መዝጋት ግዴታ ነው” የሚሉ ፈትዋዎችን የሰጡት፡፡
የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች፣ ሱፐር ማርኬትና ዳቦ ቤቶችም ቢሆን እየሸጡለት ያለው ግለሰብ ጾምን ለመተው በቂ ምክንያት የሌለው ከመሆኑ ጋር ቀን ላይ ሊበላው እንደሆነ ከሁኔታው ካወቁ ወይም በአመዛኙ ከገመቱ ለርሱ መሸጥ አይፈቀድላቸውም፡፡
ያ ዐብደላህ፥ ሪዝቅ የሚሰጠው አላህ ነው፤ እሱን እያመጹ የሚገኝ ገቢ በረካም አይኖረውም፡፡
የሥራ ዘርፍ መቀየር ወይም ደግሞ ረመዷን ላይ ማምሻውን ብቻ በመስራት በትንሹ መብቃቃትና ወንጀለኛ የማያደርጉ የግብይት ዓይነቶችን ብቻ እየለዩ መጠቀም (ቀን ላይ ለማይመገቡት፣ ለሕፃናትና በበቂ ምክንያት መጾም ግዴታ ለማይሆንባቸው ብቻ መሸጥ) መሰል መፍትሄዎችን መጠቀም ይገባል፡፡
ምን ችግር አለው!? ሀገራችን ላይ የተለመደ ተግባር ነው! ታድያ ድሃ ምን ሰርቶ ይብላ/ እንዴት ይኑር? እኛ ሃገር ላይ ይህን ማድረግ ይከብዳል... ወዘተ ማለት አላህ ዘንድ ከመጠየቅ አያድኑም፡፡
“እኔን ምን አገባኝ? ሁሉም በስራው እራሱ ነው የሚጠየቀው” የሚል የአላዋቂ ንግግር የሚናገሩ ሰዎችም አሉ! ከላይ እንደተገለጸው ረመዷን ቀን ላይ ያለበቂ ምክንያት መብላት ከዝሙትና መሰል ወንጀሎች የከፋ ተግባር ነው፤ ታድያ ዝሙት ለሚሰራ ሰው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ምንም ችግር የለውም ማለት ነው?! ሱብሓነላህ! አላህ በተከበረው ቃሉ የሚከተለውን ብሏል፥
(وَتَعَاوَنُواْ عَلَى ٱلۡبِرِّ وَٱلتَّقۡوَىٰۖ وَلَا تَعَاوَنُواْ عَلَى ٱلۡإِثۡمِ وَٱلۡعُدۡوَٰنِۚ وَٱتَّقُواْ ٱللَّهَۖ إِنَّ ٱللَّهَ شَدِيدُ ٱلۡعِقَابِ 2 ) [المائدة: 2]
“በመልካም ስራና ወንጀልን በማስወገድ (አላህን በመፍራት) ተባበሩ፤ በወንጀልና ወሰን በማለፍ አትተባበሩ፤ አላህ ቅጣቱ ብርቱ ነውና” አል ማኢዳህ፡ 2፡፡
ይህን መልእክት ለሚመለከታቸው ሁሉ በማድረስም በመልካም የማዘዝና መጥፎን የማውገዝ ግዴታ እንወጣ፡፡
✍️ ኡስታዝ አሕመድ ሸይኽ ኣደም
ረመዷን 20/1447 ዓ.ሂ
🔵 @TewhedandSuna 🌐