ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደ ባልና ሚስት መኖር ያሉት ህጋዊ ውጤቶች
በግል ግንኙነት በኩል

በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ መሠረት ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ወንድ እና ሴት ቤተሰቦች መካከል ሕጋዊ ጋብቻ እንደፈጸሙ ሰዎች የሥጋ ዝምድና አይፈጠርም፡፡ ማለትም የሴቷ እናትና አባት ለወንዱ አማች፤ የወንዱ እናትና አባት ለሴቷ አማች አይሆኑም፡፡ በተመሳሳይ የሴት ወንድምና እህት ወይም ሌላ ማንኛውም አይነት ዘመድ አዝማድ ከወንዱ የወንዱ ደግሞ ከሴቷ ጋር በህግ የሚፈጠር ዝምድና አይኖራቸውም፡፡ ነገር ግን ወላጆችና ተወላጆች፤ ወንድምና እህት፤ አንድ ሴት ከአጎቷ ወይም አንድ ወንድ ከአክስቱ ጋር ትዳር ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት አብረው ሊኖሩ አይችሉም፡፡ በተጨማሪም በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ማለትም ከሚስት ወላጆች ወይም ተወላጆች እንዲሁም ሴቷ ከባሏ ወንድም እንዲሁም ወንዱ ከሚስቱ እህት ጋር ጋብቻ ሳይፈጽሙ አብረው መኖር አይችሉም፡፡ ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ሰዎች ሕጋዊ ጋብቻ እንደፈጸሙ ሰዎች የጋራ ወጪያቸውን ለመሸፈን እንደየአቅማቸው አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸው፡፡
በንብረት በኩል

ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ወንድ እና ሴት ለ3 /ሶስት/ አመት ያላነሰ ጊዜ አብረው ከኖሩ በዚህ ጊዜው ውስጥ ያፈሯቸው ንብረቶች በሙሉ የጋራ ሀብት ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ወንድ እና ሴት ጋብቻ ሳይፈጽሙ አብረው የኖሩት ከ3 አመት ያነሰ ከሆነ ግንኙነቱ ሲቋረጥ ሁለቱም በስማቸው የተመዘገቡ ንብረቶችን
ብቻ ይዘው የሚቆዩ ሲሆን 3 አመት ቢቆዩም አንዳቸዉ ከግንኙነቱ በፊት ያፈሩትን ሀብት ሌላኛው ሰው የመካፈል መብት የለውም፡፡

እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ሰዎች በጋራ በሁለቱም ስም ወይም በየግል ስማቸው ተመዝግቦ የሚገኝ እና ያላቸው ንብረት በሙሉ ወንዱ እና ሴቷ አብረው መኖር ከመጀመራቸው በፊት የተገኘ መሆኑ በማስረጃ ያልተረጋገጠ እንደሆነ ንብረቱን አብረው በነበሩ ጊዜ ያገኙት ነው በሚል የሕግ ግምት ይወሰዳል፡፡ ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ንብረት በተመለከተ ሕጋዊ ጋብቻ ያላቸው ሰዎች ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ ሕጎች ሁሉ ለእነርሱም ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት የጋራ ንብረት ለመሸጥ፤ ለመለወጥ፤ በመያዣ ለማስያዝ፤
ወይም ሌሎች ሰዎች በጋራ ንብረታቸው ላይ መብት እንዲያገኙ ለማድረግ፤ ከብር 500.00 /አምስት መቶ/ በላይ የሆነ ገንዘብ ለማበደር፤ ለመበደር ወይም ዋስ ለመሆን፤ ከብር 100.00 /አንድ መቶ/ በላይ የሆነ ንብረት ወይም ገንዘብ በስጦታ ለመስጠት የሁለቱም ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ የሁለቱም ፈቃድ ሳይኖር ከላይ የተደረጉት ነገሮች ተፈጽመው ቢገኙ ፈቃዱን ያልሰጠው ወገን የተፈጸመው ተግባር ወይም የተገባው ግዴታ ፈራሽ ወይም ቀሪ እንዲሆን መጠየቅ ይችላል፡፡ ይህንን ጥያቄ ለፍርድ ቤት ማቅረብ የሚቻለው ፈቃዱን ያልሰጠው ወገን ተግባሩ መፈጸሙን ባወቀ በ6 ወር ጊዜው ወይም ተግባሩ በተፈጸመ በ2 አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

በተጨማሪ ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ንብረታቸውን ከሁለት አንዳቸው ብቻ እንዲያስተዳድሩ በግልጽ ስምምነት ካላደረጉ በስተቀር ወንዱ እና ሴቷ በጋራ ንብረታቸው አብረው የሚያስተዳድሩ ሲሆን ከሁለቱ አንዳቸው ይህንን ማድረግ እንዳይችሉ የሚደርጋቸው ሁኔታ ከመጣ አንደኛቸው ብቻ ንብረቱን ያስተዳድራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ንብረቱን የሚያስተዳደረው ወገን ለሌላኛው ሰዉ መረጃ የመስጠት
ግዴታ አለበት፡፡ ገቢያቸውን በተመለከተ እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ሰዎች ገቢያቸውን ወንዱ ሴቷ እንድትቀበልለት ወይም ሴቷ ወንዱ ገቢዋን እንዲቀበልላት ሥልጣን መስጠት የሚችሉ ሲሆን ለሌላኛው ወገን ገቢ የሚቀበለው ወገን ለሚቀበለው ገንዘብ ደረሰኝ እንዲሰጥ በፍርድ ቤት ሊታዘዝ ይችላል፡፡
የጋራ ሀብት አስመልክቶ የሚደረገው ንብረት ክፍፍል በሕግ አኳያ በሕግ የተጋቡ ሰዎች ፍቺ ሲፈጽሙ ከሚያደርጉት ንብረት ክፍፍል የማይለይ ሲሆን ሁለቱም በግንኙነቱ ውስጥ የነበሩት ሰዎች የጋራ ንብረት ግማሽ ይደርሳቸዋል፡፡ ነገር ግን ግንኙነቱ የተቋረጠው በአንዱ ወገን ጥፋት ሲሆን ማለትም ወንዱ ወይም ሴቷ ታማኝ
ባለመሆናቸው ወይም በሌላኛው ላይ ሌላ በደል በማድረሳቸው ምክንያት ሲሆን እና ይህ በተጨማጭ ማስረጃ ከተረጋገጠ ጥፋት የፈጸመው ወገን ለተበዳዩ ወገን ካሳ እንዲከፍል ሊገደድ ይችላል፡፡ ይህ ካሳ የሚወሰነው
በርትእ /Equity/ የተወሰነ ገንዘብ እንዲከፍል በመወሰን ወይም ከጋራ ንብረት ላይ አብላጫውን ድርሻ ለተበደለው ወገን በመስጠት ሊሆን ይችላል፡፡

እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ሰዎች ለልጆቻቸው ለማሳደጊያ ለሚውሉ ወጪዎች ወይም የራሳቸውን ኑሮ ወጪዎች ለመሸፈን በሚል አላማ ብድር የሚበደሩ እንደሆነ ሕጋዊ ጋብቻ እንደፈጸሙ ሰዎች ሁሉ ይህ ብድር የጋራ እዳቸው ሆኖ ሁለቱም በአንድነት እና በነጠላነት የእዳው ሀላፊ ይሆናሉ፡፡ ይህ ሲባል አበዳሪዎች እዳዉን በምርጫቸው ወንዱን ወይም ሴቷን ብቻ ከፈለጉ ደግሞ ሁለቱንም በጋራ እንዲከፍሏቸው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ይህ እዳም ከሁለቱም የጋራ ንብረት ላይ፤ የጋራ ንብረቱ እዳዉን ለመክፈል በቂ ካልሆነ ደግሞ ከወንዱ ወይም ከሴቷ የግል ሀብት ላይ ተከፋይ ይሆናል፡፡

የግል እዳን በተመለከተ ደግሞ እንደባልና ሚስት የሚኖሩ ሰዎች አሁንም ከሕጋዊ ባልና ሚስት ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታቸው የግል እዳ ካለባቸው እዳው ከግል ንብረታቸው የሚከፈል ሲሆን፤ የግል ንብረታቸው እዳውን ለመክፈል በቂ ካልሆነ ግን ከጋራ ንብረታቸው ላይ የሚከፈል ይሆናል፡፡ ልጆችን በተመለከተ አንድ ወንድ እና ሴት ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት በሚኖሩ ወቅት የተረገዙ እና የተወለዱ ልጆች አባት ወንዱ ሴቷ ደግሞ እናት መሆናቸው የሕግ ግምት ይወሰዳል፡፡ በእርግጥ ይህ የሕግ ግምት በህክምና ወይም ሌላ አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ ቀሪ ሊሆን የሚችል ነው፡፡


ቸር ሰንበቱ
ፌናን ተጊበሉ
መጋቢት 17/2013 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment