የአለማቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነትና ኢትዮጵያ፡- ክፍል ሁለት
በፖለቲካዊና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ስለመሳተፍ
ተዋዋይ መንግስታት አካል ጉዳተኞች ከሌሎቹ ጋር በእኩል ደረጃ ፖለቲካዊ መብቶች እንዳሏቸውና በእነርሱ የመገልገል እድል እንደተረጋገጠላቸው ዋስትና ሰጥተው ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀጥሎ የተመለከተውን ለማከናወን ግዴታ ገብተዋል፡-
(ሀ) አካል ጉዳተኞች ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ የመምረጥና የመመረጥ መብትንና እድልን ጨምሮ ከሁሉም ይልቅ፡-
1ኛ/ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቶች፣ መገልገያዎችና ቁሳቁሶች ተገቢ፣ ምቹና ተደራሽነት ያላቸው እንዲሁም ለመረዳትና ለመጠቀም ቀላሎች እንዲሆኑ በማድረግ፣
2ኛ/ ምርጫዎችና ይፋዊ ሕዝበ-ውሳኔዎች በሚካሄዱባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ አንዳች ማስፈራራት ሳይደርስባቸው በሚስጥር የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት መሠረት ድምፅ የመስጠትና ተገቢ ሆኖ ሲገኝ የአዳዲስና ደጋፊ ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም አመቻችቶ የኃላፊነት ቦታን በተጨባጭ ለመያዝና ሁሉንም ዓይነት ሕዝባዊ ተግባራት ለመከወን በሁሉም የመንግሥት እርከኖች እጩ ተመራጭ ሆኖ የመሰለፍ መብቶችን በመጠበቅ፣
3ኛ/ መራጮች ሆነው በሚቀርቡበት ጊዜ ፈቃዳቸውን ነፃ ሆነው ይገልጹ ዘንድ ዋስትና በመስጠትና ይህንኑ ለማሳካት ጥያቄ ሲያቀርቡም እንደአስፈላጊነቱ በድምፅ አሰጣጥ ወቅት በገዛ እራሳቸው ምርጫ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኙ በመፍቀድ፣ በቀጥታም ሆነ በነፃነት በተመረጡ ወኪሎቻቸው አማካኝነት ውጤታማነቱ በተረጋገጠና በተሟላ ሁኔታ በፖለቲካዊና በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ማረጋገጥ!
(ለ) አካል ጉዳተኞች ያለ አድልዎና ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ በሕዝባዊ ጉዳዮች ክንውን ውጤታማ ሙሉ ተሳታፊዎች የሚሆኑበትን እድል በንቃት ከፍ ማድረግና
1ኛ/ በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴና አስተዳደር ረገድ ባለድርሻዎች በሆኑ ማኀበራትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ የሚደረገውን ተሳትፎና
2ኛ/ አካል ጉዳተኞችን በዓለምአቀፍ፣ በብሄራዊ፣ በአህጉራዊና በአካባቢ ደረጃ የሚወክሉ ድርጅቶችን መመስረትንና በእነዚሁ ውስጥ መግባትን ጨምሮ፣ በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎ ማበረታታት የሚል ሲሆን ለዚሁ አፈጻጸም ይረዳ ዘንድ ይመስላል
የኢፌድሪ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተደነገገ ሲሆን አካልጉዳተኞችን አስመልክቶ ጥቂት ልዩ ድንጋጌዎችን አስቀምጦ ይገኛል፡፡
ይኸውም;
1. በአንቀጽ 31/3 እጩ ሆኖ ለመቅረብ የፈለገ አካል ጉዳት አልባ ግለሰብ 5000 የድጋፍ ፊርማ ሲሆን፣ አካልጉዳተኛ ግን 3000 ብቻ ነው፤
2. በአንቀጽ 32 የእጩ አቀራረብን አስመልክቶበ32/2 በተደነገገውየፖለቲካ ‹ፓርቲዎች እጩ ሆኖ ለመቅረብ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ከሆነ፣ በሚወዳደርበት የምርጫ ክልልውስጥ ከሆኑ መራጮች ለጉዳት አልባው 2000፣ ለአካልጉዳተኛው፣ 1500 ሲሆን፤ ለክልል ምክርቤት ከሆነ ደግሞ ለጉዳት አልባው 1000፣ ለአካልጉዳተኛው 750 የዲጋፍ ፊርማ ያስፈልጋል፡፡
3. በአንቀጽ 100 ከመንግስት ለፖለቲካ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከሚታዩ መስፈርቶች መካከል-
በንዑስ 2 በፊደል ሠ የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች፣ በፊደል ረ ደግሞ የአካል ጉዳተኛ አመራሮች ብዛት የሚታይ መሆኑን እናገኛለን፡፡
በአጠቃላይ የአለማቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ባካተታቸው 35 አንቀጾች ብዙ ዝርዝር መብቶችን የደነገገሲሆን በስራ ላይከቅጥር እስከደረጃ እድገትና በተለይም በሀላፊነት ደረጃ አካልጉዳተኞችን እድል እንዲያገኙ ያለማመቻቸት፣ ከሕግ ይልቅ የግለሰቦች አመለካከትና በጎ ፈቃድ ወሳኚ መሆኑ፤ የትምህርት ተደራሽነት አሁንም ገና በጣም ገና መሆኑ፤ በሀገሪቱ በብዙ ገንዘብና ለብዙ አመታት የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ መሰረተ ልማቶች ስምምነቱንና የሀገሪቱን ህጎች አለማሟላታቸው ላይ ትኩረትና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ካልተሰራ ግንባታዎቹ እንዳልተገነቡ፣ ህጎቹም እንዳልተደነገጉ ከመቆጠር የሚያዲናቸው ጉዳይ አይኖርም፡፡
ሁላችንንም የመፍትሄ አካል የሚያደርግ ልቦና ይስጠንና ሀገራችንንም ሆነ ከተማችንን ለሁሉምና እኛም በየትኛውም የጤናና የእድሜ ዘመናችን ልንኖርባቸው የንችል አድርገን ለመገንባት ያብቃን፡፡
ቸር ይግጠመን፡፡
ሲሳይ ሰማኝ
የካቲት 19/2013 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment