👉በሕንፃ ግንባታ የሚደርሱ አደጋዎች ከትራፊክ አደጋ ቀጥሎ የከፉ መሆናቸው ተነገረ

⚡️በጥንቃቄ ጉድለት 142 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል

📍‹‹ከሚያማምሩ ሕንፃዎች ጀርባ የብዙ ወንድምና እህቶቻችን ደም ያላግባብ ፈሷል›› የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን

🏷በኢትዮጵያ ከትራፊክ አደጋ ቀጥሎ ጥንቃቄ በጎደለው የሕንፃ ግንባታ ምክንያት፣ በሰዎች ላይእየደረሱ ያሉ አደጋዎች እየጨመሩና እየከፉ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

⏺ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበርና ከኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ጋር የግንባታ ሒደትንና ደኅንነትን በተመለከተ ሐሙስ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ባደረጉት ውይይት ላይ የአደጋው አስከፊነት መገለጹን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

⏺የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ኢንጂነር) ባቀረቡት መረጃ፣ ከትራፊክ አደጋ ቀጥሎ በኮንስትራክሽን ሳይቶች ጥንቃቄ በጎደለው አሠራር ግድፈት ምክንያት እየደረሱ ያሉ አደጋዎች እየጨመሩና እየከፉ ናቸው ብለዋል፡፡ በኮንስትራክሽን የግንባታ ሥፍራዎች የሚደርሱ አደጋዎች እየታፈኑ በሽምግልናና በሌሎች መንገዶች ስለሚድበሰበሱ ለፖሊስ እየተገለጹ አለመሆናቸውን ገልጸው፣ እየደረሰ ያለው የሕይወት መቀጠፍ ጉዳይ ያሳስባል ብለዋል፡፡

▶️ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ከሚያልፈው ሕይወት በተጨማሪም በመኖሪያ አካባቢዎች ሌሊት መሬት በማሽነሪ እየተቆፈረ ሰዎች እየተረበሹ መሆናቸውን ገልጸው፣ ‹‹የሌሊት ሥራን ባልቃወምም የሰው ልጅ በሚያርፍበት ሰዓት ደኅንነቱንና ሰላሙን መንሳት ተገቢ ባለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

📍የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥርባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳሬክተር አበበ እሸቴ (ኢንጂነር) ባቀረቡት ጽሑፍ፣ በግንባታ ሒደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ዘርዝረዋል፡፡

በተጠናቀቀው የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከ11,000 በላይ ሕንፃዎች ፈቃድ ወስደው ወደ ግንባታ መግባታቸውን፣ በተመሳሳይ ከ2017 ዓ.ም. ቀድሞ ወደ ሥራ የገቡ ከ12,000 በላይ ግንባታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ሥር በግንባታ ላይ የሚገኙ ሕንፃዎች አጠቃላይ ግምታዊ ዋጋቸው ከ5ዐዐ ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ብለዋል፡፡

በግንባታዎች ሥፍራ በቸልተኝነት ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ስለሆነ፣ ችግሩን ለመለየት ባለፉት ሦስትና አራት ወራት ባለሥልጣኑ ጥናት ማካሄዱን ተናግረዋል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ መሠረት የበሰበሰ እንጨት በመጠቀም ከሚሠሩ መወጣጫዎች መውደቅ፣ ለሊፍት ተብለው የተቀመጡ ክፍት ቦታዎች ውስጥ መግባት፣ ሕንፃዎችን ተጠግቶ በሚያልፍ የኤሌክትሪክ መስመር የሚደርስ አደጋ፣ መብራት ሳያጠፉ እየሠሩ በድንገት የሚሞቱ፣ ከፎቅ አናት ላይ ብረት፣ ብሎኬትና እንጨቶች እየወደቁ በሚያደርሱት አደጋ ቀለል የማይባል ሕይወት ተቀጥፏል ብለዋል፡፡

በግንባታ መዋቅሮች ችግር በተለይም የአፈርመናድን የሚከላከሉ መዋቅሮች ደረጃና ጥራታቸው ተጠብቆ አለመገንባት ምክንያት ሕይወት እየተቀጠፈ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አብዛኞቹ የሕንፃ ግንባታዎች የደኅንነት ዕውቀት ባላቸው ይከናወናሉ ብሎ መናገር ያስቸግራል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ የግል የደኅንነት መጠበቂያ መሣሪያዎችን በአግባቡ አለመጠቀምና የግንባታ ባለሙያዎች ስለደኅንነት መጠበቂያ መሣሪያዎች ዕውቀቱ ስለሌላቸው እየተጠቀሟቸው አይደለም ብለዋል፡፡

በአማካሪዎችና በኮንትራክተሮች የሚደረገው የቁጥጥር ማነስና ለግንባታ ደኅንነት በቂ የሆነ ገንዘብ አለመመደብ ሌላው ችግር መሆኑን ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአንድ ሕንፃ ግንባታ የደኅንነት ወጪ ከአጠቃላይ የግንባታ ዋጋው ከዐ.8 እስከ አምስት በመቶ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ ይህ እየተደረገ ባለመሆኑ ችግሮች እያጋጠሙ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡

በሕንፃ በግንባታ ወቅት ከደረሱ አደጋዎች መካከል ከ2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. በነበሩት ጊዜያት፣ ከፖሊስና ከጤና ተቋማት ተወስደው በተመዘገቡ መረጃዎች መሠረት ብቻ የ142 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል ብለዋል፡፡
ďťż
በአደጋው ስፋት በተለይ ለሚ ኩራና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ መረጃው ለመንግሥትና ለፀጥታ አካላት ሳይደርስና ሳይመዘገብ የቀረ፣ እንዲሁም በሕክምና ወደ አገር ቤት የሄዱ፣ ቤት ውስጥ ለሕክምና ተወስደው በዚያው የሞቱና በተለያዩ መንገዶች ያልተመዘገቡ ቁጥራቸው እንደማይታወቅ አስረድተዋል፡፡

ከአደጋዎቹ መካካል ፒያሳ አካባቢ በግንባታ ላይ ያለ ሕንፃ በመፍረሱና በመደርመሱ ስምንት ሰዎች መሞታቸው፣ በኮልፌ ቀራኒዮ አካባቢ በኤሌክትሪክ ንክኪ የሞቱ መኖራቸው፣ ከመወጣጫ ወድቀው የሞቱና በካዛንችስ ቁፋሮ ላይ የነበረ ቦታ በመደርመሱ የሞቱ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የበሰበሰ የእንጨት መወጣጫ ምክንያት መሞታቸውን፣ የግንባታ ቦታው በተገቢው ሳይዘጋጅ ሠራተኞች በወዳደቁና መሬት ላይ በተተከሉ ቁርጥራጭ ብረቶች ምክንያት አደጋ መድረሱን፣ ሠራተኞች መንቀሳቀስ የማይችልባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተገነቡ ከሚገኙ ሕንፃዎች ውስጥ 3,544 የሚሆኑት ምንም ዓይነት የደኅንነት ቅድመ ጥንቃቄ የማይከተሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ግንባታዎቹ አደገኛ ተብለው የተፈረጁ ናቸው ብለዋል፡፡

ከወንጀል ተጠያቂነት አንፃር ሕጉ አማካሪ፣ ኮንትራክተርና ባለቤቱን ከአምስት ዓመታት እስከ 15 ዓመታት እስራትና ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣቶች እንደሚያስከትል ገልጸው፣ ወደ ቅጣት ከመገባቱ በፊት ግን ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት ተገቢውን ሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠትና በቂ የሆነው የግንባታ ደኅንነት መጠበቂያ ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በግንባታ ቦታዎች የሚደርሱ አደጋዎችን ሪፖርት ማድረግ የለም ማለት ይቻላል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኮንትራክተሩ አደጋ የደረሰበትን ሰው ወይም የሞተን ሰው ጠቅልሎ ወደ ቀብር ቦታ ቢወስድ ይሻለዋል እንጂ በፍፁም ሪፖርት እየተደረገ አይደለም ብለዋል፡፡ ለአካባቢ ፖሊስ ወይም ለወረዳ የጤና መዋቅር አምቡላንስ ሲደወል እንጂ አደጋዎች ሪፖርት እየተደረጉ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሕይወት ሳሙኤል (ኢንጂነር) በበኩላቸው በየዕለቱ በሚባል ደረጃ ሕይወት እንደሚጠፋ ገልጸው፣ ከላይ የቀረበው ድምር የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ገላጭ አይደለም ብለዋል፡፡

አደጋው ከደረሰ በኋላ የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ሪፖርት ሳይደረጉ በሽምግልና የቀሩ በርካታ መሆናቸውን ገልጸው፣ ‹‹ከሚያማምሩ ሕንፃዎች ጀርባ የብዙ ወንድምና እህቶችን ደም ያላግባብ ፈሷል፡፡ ሕይወት ያላግባብ አልፏል፤›› በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ ወደ ተቋሙ በኃላፊነት በመጡባቸው የመጀመሪያዎቹ ወራት በቀን ከፖሊስ በሚመጡ ሪፖርቶች፣ በግንባታ ወቅት የአንድ ወይም የሁለት ሰው ሕይወት በማለፉ ምክንያት ማብራሪያ እንድንሰጥ እንጠይቅ ነበር ብለዋል።

Via Reporter

@etconp

Comments

Be the first to add a comment