የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ጉዲፈቻ
ጉዲፈቻ የሚለው ቃል ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀጥታ ወደ አማርኛ የተወሰደ ሲሆን ፍቺውም ከሌላ አብራክ የተገኘን ልጅ ከሌላ ሰው የተወለደ መሆኑን አምኖና ተቀብሎ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቱን ጠብቆ እንደ ገዛ ልጅ አድርጎ ማሳደግ ማለት ነው፡፡
ጉዲፈቻ የሚለው ቃል የእንግሊዝኛ አቻው “Adoption” ሲሆን አመጣጡም “ad-optare” ከሚል የላቲን ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም “መምረጥ” የሚል ነው፡፡ ይህም ጉዲፈቻ በጉዲፈቻ አድራጊው ምርጫ ብቻ የሚከናወን መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ጉዲፈቻ አድራጊው በነፃ ፈቃዱ ከሌላ አብራክ የተገኘን ልጅ ለማሳደግና ለመጠበቅ እንዲሁም ለእድገቱ አስፈላጊ የሆኑትን ማናቸውም እንክብካቤዎች ለማድረግ ወስኖ የሚወስደው እርምጃ ሲሆን ይህም ልጁ የጉዲፈቻ አድራጊውን ቤተሰብ ስም፣ ንብረትና ህይወት እንዲካፈል የሚያደርግ መብት ያጎናጽፈዋል፡፡ ከአብራኩ ክፋይ የተገኘው ልጅ ያለው ማንኛውም መብት ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ ጉዲፈቻ አንድ ሰው ቀደም ሲል የነበረውን ቤተሰባዊ የደም ትስስር በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በአዲስ ቤተሰባዊ ትስስር የሚተካ ወይም የሚለውጥ ማህበራዊ ተቋም ነው ሊባል ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ ጉዲፈቻ በትክክል መቼ እንደተጀመረ የሚጠቁም ጥናት ባይገኝም ከ1800 ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በባሕላዊ መንገድ ይካሔድ እንደነበር ይገመታል፡፡ በተለይ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዘንድ ይተገበር እንደነበርም ይነገራል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕግ ማዕቀፍ የተበጀለት በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ሲሆን በዚህ ሕግ ስለ ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ በግልፅ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ፣ በፍትሐብሔር ሕግ ውስጥ ያለውን የቤተሰብ ሕግ ክፍል ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት ጋር አጣጥሞ ማሻሻል አስፈጓል፡፡ በዚህም መሰረት የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 213/1992 ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ፀንቶ በስራ ላይ ውሏል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በምዕራፍ አሥር ስለ ጉዲፈቻ በዝርዝር የሚደነግግ ሲሆን፣ በአንድ ሰውና በአንድ ልጅ መካከል በሚደረግ ስምምነት የጉዲፈቻ ዝምድና ሊፈጠር እንደሚችል በአንቀጽ 180 ስር ይደነግጋል፡፡ ሕጉ የጉዲፈቻ ሥርዓት አፈጻጸም መሠረታውያንን ማለትም የዕድሜ ገደብ፣ የስምምነት አሰጣጥ፣ የባለድርሻ አካላትን ሚና በዝርዝር ደንግጓል፡፡
በዚህ ህግ ሕፃናት/ልጆች ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ዜግነት ባላቸው የጉዲፈቻ አድራጊዎች በስምምነት ሊሰጡ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 193 እና 194 ላይ የውጭ ጉዲፈቻ እንደ አማራጭ መቀመጡ በህፃናቱ ላይ የተለያየ የማንነት ጥያቄዎችና ችገሮችን ከመፍጠሩ ባሻገር በህፃናት ላይ ለሚፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎች በር እየከፈተ በመምጣቱ በ2010ዓ.ም የወጣዉ አዋጅ ቁጥር 1070/2010 የቤተሰብ ህጉን በማሻሻል አገራችን የውጭ ጉዲፈቻ ስርዓትን እንድታስቀር/እንደትከለክል አድርጓል። ኢትዮጵያ ህፃናትን ለውጭ አገራት ዜጎች በማደጎነት በመስጠት ከሚታወቁ አስር የዓለም አገሮች አንዷ እንደነበረችም መረጃዎች የሚጠቁሙ ቢሆንም አሁን ላይ ከዚህ አዋጅ መዉጣት በኃላ በውጭ አገራት ዜጎች የሚደረግ የጉዲፈቻ ስርዓት ቆሟል፡፡
በተሻሻለዉ የቤተሰብ ህግ መሰረት የጉዲፈቻ ዝምድና በጉዲፈቻ አድራጊዉና በጉዲፈቻ ልጁ ማለትም በአሳዳሪዉ በኩል በሚደረግ ስምምነት የሚፈጸም ሲሆን ይህ ስምምት ዉጤት እንዲኖረዉ በፍርድ ቤት ቀርቦ መጽደቅ ይኖርበታል (አንቀጽ 180፣190 እና 194(1))፡፡ አንድ ልጅ በባልና ሚስት ጉዲፈቻ ከሚደረግበት ሁኔታ በስተቀር በአንድ ጊዜ ለብዙ ሰዎች የጉዲፈቻ ልጅ ሊሆን አይችልም፡፡
የጉዲፈቻ ዉጤትን ስንመለከት ጉዲፈቻ የተደረገ ልጅ ከጉዲፈቻ አድራጊዉ ልጅ ጋር ተመሳሳይ መብት ያለዉ እንደሆነ ልጅ ይቆጠራል(አንቀጽ 181)፡፡ ይህ ማለት የጉዲፈቻ ልጅ እንደማንኛዉም የተፈጥሮ ልጅ ከጉዲፈቻ ቤተሰቦቹ ጋር ህጋዊ ትስስር የሚኖረዉ እንደሆነ ዉርስን ጨምሮ ሌሎች ህጋዊ መብቶች ይኖረዋል፡፡ ምንም እንኳን የጉዲፈቻ ልጁ የጉዲፈቻ አድራጊዉ ልጅ እንደሆነ የሚቆጠር ቢሆንም ከተፈጥሮ ወላጆቹ ጋር የነበረዉን ዝምድናና ትስስር ይዞ የሚቀጥል ሲሆን ሆኖም አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮ ከሁለት አንዱን መምረጥ ካለበት ከተፈጥሮ ቤተሰቦቹ ይልቅ የጉዲፈቻ ቤተሰቦቹ ሊመረጡ እንደሚገባ ህጉ ደንግጓል (አንቀጽ 183)፡፡
ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆችን ወይም ወደ ጎን የሚቆጠሩ ዘመዶችን በሚመለከት ጉዲፈቻዉን በግልጽ የተቃወሙና ይህንን ተቃዉሟቸዉን የጉዲፈቻ ስምምነቱ በፍርድ ቤት መጽደቁን ባወቁ በአንድ አመት ጊዜ ዉስጥ በፍርድ ቤት መዝገብ ካስመዘገቡ የጉዲፈቻዉ ስምምነት ወይም ዝምድና በእነሱ ላይ ዉጤት አይኖረዉም(አንቀጽ 182)፡፡
አንድ ሰዉ በጉዲፈቻ አድራጊነት ልጅ ወስዶ ለማሳደግ በእድሜ መብሰል አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት በቀድሞ ሕግ ላይ 18 አመት የነበረዉን ዝቅተኛ እድሜ ከፍ በማድረግ የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 184(1) የጉዲፈቻ አድራጊዉ ዝቅተኛዉ እድሜ 25 አመት እንዲሆን ደንግጓል፡፡ ጉዲፈቻ አድራጊዎቹ ባልና ሚስት ከሆኑ የአንዳቸዉ እድሜ 25 አመት የሞላ ከሆነ በቂ ነዉ፡፡ በባልና ሚስት አማካኝነት የሚደረግ ጉዲፈቻ ልጁ ከሁለት ያንዳቸዉ ልጅ ካልሆነ በስተቀር ሁሌም ቢሆን የሁለቱ ስምምነት መኖር ያስፈልጋል (አንቀጽ 186)፡፡
የጉዲፈቻ ተደራጊ ልጅ የእድሜ ጣሪያን በተመለከተ ከጉዲፈቻ ስርዓት አላማና ግብ ማለትም አካለመጠን ያልደረሱ ሰዎች ጥቅምና ደህንነትን መጠበቅ ከሚለዉ አንጻር እድሜዉ ከ18 አመት በታች የሆነና ከሞግዚት አስተዳደር ነጻ ያልወጣ ማንኛዉም ሰዉ የጉዲፈቻ ልጅ መሆን ይችላል፡፡ ሌላዉ ጉዲፈቻ በዋናነት የህጻኑን ጥቅም ከማስጠበቅ ረገድ የሚደረግ እንደመሆኑ ሕጉ በአንቀጽ 187(1) ስር የተጸነሰ ልጅ የጉዲፈቻ ልጅ መሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ሆኖም በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት እናትዬዉ ልጁን ከወለደች በኃላ እስከ ስድስት ወር ባለዉ ግዜ ድረስ ሃሳቧን ለመቀየርና ስምምነቱን ለማፍረስ ትችላለች፡፡
አንድ ልጅ የጉዲፈቻ ልጅ ለመሆን ወላጆቹ በህይወት ያሉና የሚታወቁ ከሆነ የወላጆቹ ወይም አንዱ ከሌለ የሌላኛዉ ፈቃድ ያስፈልጋል (አንቀጽ 191)፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የመንግስት ወይም የግል አሳዳጊ ተቋሞች እያሳደጉ ያሉትን ማንኛዉንም ልጅ ለጉዲፈቻ አድራጊዎች በስምምነት መስጠት ይችላሉ (አንቀጽ 192)፡፡
የጉዲፈቻ አድራጊዉ በጉዲፈቻ የተቀበለዉን ልጅ እንደልጁ በማሳደግ ፋንታ በባሪያነት ወይም በመሰል ሁኔታ ወይም ከግብረ ገብ ዉጪ ተግባሮች እንዲሰማራ በማድረግ መጠቀሚያ ያደረገዉ እንደሆነ ወይም በማናቸዉም ሌላ መንገድ የልጁን የወደፊት ሕይወት ክፉኛ በሚጎዳ አኳኋን የያዘዉ ከሆነ ልጁ በራሱ፣ ጉዳዩን ለመከታተል ስልጣን በተሰጠዉ የመንግስት አካል ወይም ጉዳዩ ያገባኛል በሚል ማንኛዉም ሰዉ አቤቱታ አቅራቢነት የጉዲፈቻ ስምምነቱ በፍርድ ቤት ሊሰረዝ ይችላል፡፡
ቸር ሰንብቱ
ፌናን ተጊበሉ
ጥር 04/2013 ዓ.ም
Comments
Be the first to add a comment