👉የግንባታ ፕሮጀክት ፊዚካል አፈጻጸም መለኪያ ስታንዳርድ ይፋ ተደረገ።

​ለሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት አዲስ የፕሮጀክት ፊዚካል አፈጻጸም መለኪያ ስታንዳርድ ዛሬ ነሐሴ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ ተደረገ።

​በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የዘርፉ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አዲስ የተዘጋጀው የስታንዳርድ ማዕቀፍ አዲስ አበባ በሚገኘው ሀርመኒ ሆቴል ላይ በተዘጋጀ መድረክ ይፋ ተደርጓል።

​በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር)፤ ስታንዳርዱ የአንድ ፕሮጀክት አፈጻጸምን ብቻ ለመለካት ሳይሆን፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ብቃት፣ ምርታማነት፣ ጥራትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

​ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚኖረው ቁልፍ ጠቀሜታዎች፦

​የፕሮጀክት መዘግየትን መቀነስ፦ የግንባታ ስራዎች በታቀደላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቁ በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል።

​ምርታማነትንና ጥራትን ማሳደግ፦

ሀገራዊ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን አጠቃላይ ብቃት በማሳደግ የሥራ ጥራት ደረጃዎች እንዲከበሩ ያደርጋል።

​ተጠያቂነትን ማስፈን፦

በግንባታ ሂደቶች ላይ ግልጽነትን በመፍጠርና የክትትል ስርዓትን በማጠናከር ተጠያቂነትን ያሰፍናል።

​የኢንቨስትመንት እምነትን ማሳደግ፦ የኢንዱስትሪውን መረጃ አስተማማኝ በማድረግ ባለሀብቶችና አጋር አካላት በዘርፉ ላይ ያላቸውን እምነት ከፍ ያደርጋል።

​ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፦ የኮንትራክተሮችን አቅም በማሻሻል አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ተወዳዳሪነታቸውን ያጠናክራል።

​የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የተሰጠውን ተልዕኮና ኃላፊነት በብቃት ለመፈጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመደመር መርህ በጋራ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መስፍን፤ በአገር አቀፍ የዘርፉ ደረጃ አዲስ የሆነው የግንባታ ፕሮጀክቶች ፊዚካል አፈጻጸም መለኪያ ስታንዳርድ ማዕቀፍ እውን እንዲሆን ተቋሙ የአጋርነት ሚና መጫወቱን አንስተዋል።

​በቀጣይም የስታንዳርድ ማዕቀፉ ወደ መሬት ወርዶ ውጤታማ እንዲሆን ባለስልጣን ተቋሙ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ የዘርፉ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላትም ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

@etconp

Comments

Be the first to add a comment