የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የክስና የቅጣት ይርጋ
ሰላም ከወንጀልና ከወንጀለኝነት እንዲጠብቀወት ከልቤ ባሉበት እየተመኘሁ!!
በዚች መልዕክት በወንጀል ሕጋችን ስለፍርድና ቅጣት ይርጋ መታገድ የተደነገገውን በጥቂቱ ሙሉውን ከመጽሀፉ እንዲያነቡት ለማነሳሳት በጣም በትንሹ እነሆ፡!!
ንዑስ ክፍል አንድ የክስ ይርጋ
አንቀጽ 216 መርህ እና ውጤቱ
1. በሕግ በሌላ አኳኋን (በልጦ ወይም አንሶ) ካልተደነገገ በስተቀር ከዚህ በታች የተመለከተው የይርጋ ዘመን ካለፈ በኋላ በማናቸውም ወንጀል የግል አቤቱታን ወይም የወንጀል ክስን መቀበልና ጉዳዩን በዳኝነት ማየት አይቻልም፡፡
የይርጋ ዘመኑ ማለፍ ለማናቸውም የወንጀል ተካፋይ ቅጣትን ያስቀራል፡፡ ለይርጋ የተወሰነም ጊዜ ካለፈ የጥፋተኛነት ውሳኔ ወይም ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ ሊወሰን አይቻልም፡፡
2. ክሱ በይርጋ ስለመታገዱና ክሱን ለመቀበል የማይገባ ስለመሆኑ ተከሳሹ ባያመለክትም ዐቃቤ ሕጉ ወይም ፍርድ ቤት በማናቸውም ጊዜ ማንሳት አለበት፡፡
አንቀጽ 217 መደበኛ የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን
1. በወንጀል ተግባር ክስ የማቅረብ የይርጋ ዘመን የሚፀናው፡-
ሀ/ የሞት ፍርድ ወይም የዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ለሚያስቀጣ ወንጀል ሃያ አምስት ዓመት፣
ለ/ ከአሥር ዓመት በላይ እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ሃያ ዓመት፣
ሐ/ ከአምስት ዓመት በላይ እስከ አሥር ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ አሥራ አምስት ዓመት፣
መ/ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል አሥር ዓመት፣
ሠ/ ከአንድ ዓመት በላይ በቀላል እሥራት ለሚያስቀጣ ወንጀል አምስት ዓመት፣
ረ/ እስከ አንድ ዓመት በቀላል እሥራት ለሚያስቀጣ ወይም በመቀጮ ብቻ ለሚያስቀጣ ወንጀል ሦስት ዓመት፡፡
2 ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው ሲገኙ፡-
ሀ/ የወንጀሎቹ ከፍተኛ ቅጣቶች ተመሳሳይ በሚሆኑበት ጊዜ የአንዱ ወንጀል የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን በሁሉም ወንጀሎች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
ለ/ የወንጀሎቹ ከፍተኛ ቅጣቶች የተለያዩ በሚሆንበት ጊዜ ከሁሉም ከባድ የሆነው ወንጀል የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን በሌሎች ወንጀሎች ላይም ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
አንቀጽ 218 ልዩ የግል አቤቱታ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን
የአንቀጽ 213 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጣ የማናቸውም የወንጀል ክስ የይርጋ ዘመን ሁለት ዓመት ነው፡፡
አንቀጽ 219 የይርጋ ዘመን አቆጣጠር
1 የይርጋ ዘመን የሚታሰበው የቅጣት ማክበጃ ወይም ማቅለያ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ሳይገቡ በዚህ ሕግ ልዩ ክፍል የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
የተፈፀመው ወንጀል በተለዋጭ ወይም በተደራራቢ ተፈፃሚነት በሚኖራቸው ቅጣቶች የሚያስቀጣ ሲሆን የይርጋ ዘመኑ የሚታሰበው ከሁሉም ከባድ ለሆነው ወንጀል በዚህ ሕግ ልዩ ክፍል የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
2 የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው ጥፋተኛው የወንጀሉን ድርጊት ከፈጸመበት ቀን አንስቶ ነው፡፡
የወንጀሉ ድርጊት እየተደጋገመ ተፈፅሞ እንደሆነ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀመረው የመጨረሻው የወንጀል ድርጊት ከተፈፀመበት ቀን አንስቶ ነው፡፡ እንዲሁም የወንጀሉ ድርጊት ለረጅም ጊዜ ሲፈፀም የቆየ እንደሆነ የየርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው የወንጀሉ ድርጊት ካቆመበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡
ወንጀሉ ተደርጓል ለማለት የሚቻለው ከጠባዮቹ አንዱ የወንጀሉ ውጤት የሆነ እንደሆነ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው የወንጀሉ ውጤት ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
አንቀጽ 220 የይርጋ ዘመን መታገድ
1 በሕጉ ወይም በፍሬ ነገር ክሱ እንዳይጀመር ወይም እንዳይቀጥል የሚያግድ መሰናክል እስካለ ድረስ የይርጋ ዘመን መቆጠሩ ታግዶ ይቆያል፡፡
እንዲሁም ክስ ቀርቦ ነገሩ በዳኝነት በመታየት ላይ እንደሆነ ወይም በሌላው ችሎት የቀረበው ክስ ሳይፈፀም ተከሳሹ በተከሰሰበት የወንጀል ክስ ላይ ውሳኔ ሊሰጥ የማይገባ እንደሆነ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር ታግዶ ይቆያል፡፡
መሰናክሉም እንደተወገደ ወዲያውኑ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር ይቀጥላል፡፡
2 ስለክሱ መከታተል አቤቱታ እንዲቀርብ ማስፈለጉ በሕግ ተመልክቶ በተገኘ ጊዜ አቤቱታ አለማቅረቡ የይርጋውን መቆጠር አያግደውም፡፡
እንዲሁም ክሱ እንዳይጀምር ወይም እንዳይቀጥል ጥፋተኛው በራሱ ፍላጐት የሚፈፅመው ተግባር የይርጋ ጊዜውን መቆጠር አያግደውም፡፡
አንቀጽ 221 የይርጋ ዘመን መቋረጥ
ከወንጀሉ ወይም ከወንጀለኞቹ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ብርበራ እንዲደረግ፣ መጥሪያ እንዲሰጥ ወይም ክስ እንዲቀርብ የሚሰጥ ትዕዛዝ፣ የሚፈፀም ድርጊት ወይም የሚሰጥ ውሳኔ የይርጋ ዘመኑን መቆጠር ያቋርጣል፡፡
የይርጋ ዘመኑ መቋረጥ ፍጹም የሆነ ውጤት አለው፤ በወንጀሉ ተካፋይ መሆናቸው ለታወቀውም ሆነ ላልታወቀው ሁሉ መቋረጡ ይፀናባቸዋል፡፡
አንቀጽ 222 ፍፁም የሆነ የይርጋ ዘመን
በማናቸውም ምክንያት መደበኛ የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን /አንቀጽ 217/ አጠፌታ ጊዜ ካለፈ ወይም ልዩ የግል አቤቱታ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን ሲሆን /አንቀጽ 218/ ከዚሁ ዘመን በግማሽ የሚበልጥ ጊዜ አልፎ እንደሆነ በወንጀሉ ላይ የሚቀርበው ክስ ወይም የሚደረገው መከታተል በይርጋ ቀሪ ይሆናል፡፡
ንዑስ ክፍል ሁለት የቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃዎች ይርጋ
አንቀጽ 223 መርህ እና ውጤቱ
1. በሕግ በሌላ አኳኋን በግልጽ ካልተደነገገ በስተቀር በተቀጪው ላይ የተወሰነው ቅጣት በማናቸውም በተቀጪው ላይ የተወሰነው ቅጣት በማናቸውም ምክንያት ከዚህ በታች ከአንቀጽ 224‐228 በተመለከቱት ጊዜያት ውስጥ ሳይፈጸም የቆየ እንደሆነ ቅጣቱን የማስፈጸም መብት ቀሪ ይሆናል፤ የተወሰነውም ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ ሊፈጸም አይችልም፡፡
የዋነኛው ቅጣት የይርጋ ዘመን የተጨማሪ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎች መፈፀምንም ያስቀራል፡፡ እንዲሁም የዋናው ቅጣት የይርጋ ዘመን ከቅጣቱ ጋር ለተያያዘ የንብረት መውረስ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም የጥንቃቄ እርምጃዎች ያለዋነኛ ቅጣት በሚወሰኑበት ጊዜ የአንቀጽ 224(1)(መ) ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
2. ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዳኝነት ወይም የአስተዳደር ባለሥልጣኖች በራሳቸው ተነሳሽነት የቅጣት የይርጋ ደንብን አክብሮ የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
3. የተወሰነው ቅጣት በይርጋ ዘመኑ መታገድ ምክንያት ሳይፈፀም ቢቀርም በወንጀለኞች መዝገብ ውስጥ እንደተመዘገበ ይቆያል፡፡
አንቀጽ 224 መደበኛ የቅጣት ይርጋ ዘመን
1. የቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃዎች ይርጋ ዘመን የሚፀናው በሚከተለው ሁኔታ ይሆናል፤
ሀ/ ለሞት ፍርድ፣ ወይም ለዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ሰላሳ ዓመት
ለ/ ከአሥር ዓመት በላይ ለሆነ ነፃነትን የማሳጣት ቅጣት ሃያ ዓመት
ሐ/ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ነፃነትን የማሳጣት ቅጣት አሥር ዓመት
መ/ ሰማናቸውም ሌላ ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ ውሳኔ አምስት ዓመት
2. ተደራራቢ ቅጣቶች ተወስነው እንደሆነ ቀላል የሆኑት ቅጣቶች በይርጋ ቀሪ የሚሆኑት ከሁሎም ከባድ የሆነው ቅጣት በይርጋ ቀሪ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡
አንቀጽ 225 የቅጣት የይርጋ ዘመን አቆጣጠር
Comments
Be the first to add a comment