የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 2ዐ (6) ይግባኝ ከመሠረታዊ መብቶች አንዱ አድርጎ ያስቀመጠዋል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 9 (4) ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የሐገሪቱ ሕግ አካል እንደሆኑ ይገልፃል፡፡
ይግባኝ መቼ እና እንዴት ይቀርባል ?
ይግባኝ የሚጠየቀው በመጀመሪያው ፍርድ ወይም ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል እነደሆነ ተመልክተናል፡፡ ይግባኝ የሚቀርብባቸው አቤቱታዎች በመጨረሻ ፍርድ ወይም ውሣኔ ያላገኙ ጉዳዮች ( Inter-Locutory Issues ) መሆን የለባቸውም፡፡ ባለጉዳዮች የተበጣጠሱ ጉዳዮችን ይዘው ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት የሚመጡ ከሆነ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤቱ ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ ፍ/ቤቶቹ በሚሰጡት ቁጥር ስፍር የሌለው ትዕዛዝ በስር ፍ/ቤቶች እየተካሄደ ያለን የፍትህ ሥርዓት ሊያውከው ስለሚችል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪInter-Locutory ጉዳዮች ይግባኝ የማይቀርብባቸው ለጊዜው እንጂ ከዋናው ጉዳይ ጋር ተጠቃለው ይግባኝ ሊባልባቸው እንደሚችል በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 32ዐ /3/ ላይ ተመልክቷል፡፡በወንጀል ጉዳይ ይግባኝ የሚል አካል ፍርዱ በተሰጠ በ15 ቀን ውስጥ በፅሁፍ ማስታወቅ እንዳለበት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 187 (1) የተደነገገ ሲሆን ይግባኝ ባዩ የፍርዱ ግልባጭ በደረሰው በ3ዐ ቀን ውስጥ ቅሬታውን ( የይግባኝ ማመልከቻውን ) አዘጋጅቶ መላክ አለበት፡፡
በፍትሐብሔር ጉዳይ ሲሆን ግን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 123 /2/ እንደተመለከተው ፍርዱ በተሰጠ በ6ዐ ቀን ውስጥ ይግባኙ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት መቅረብ መቻል አለበት፡፡ በሕጉ የተፈቀደው ጊዜ ካለፈ በወንጀልም ሆነ በፍትሃብሔር በቂ ምክንያት በማቅረብ ሲፈቀድ ነው ይግባኝ ሊቀርብ የሚችለው፡፡
በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት መሠረት ይግባኝ መብት ቢሆንም በጊዜ እና በእርከን ሊገደብ እንደሚችል ነው ዳኛ ፀጋይና ዳኛ ሽመክት የሚገለፁት፡፡ በጊዜ የተባለው ከላይ የተገለፀው ሲሆን በእርከን የተገደበው ደግሞ ከአንድ ጊዜ በላይ ይግባኝ ማለት የማይቻልበት ሁኔታ ስላለ ነው፡፡ ይህም ማለት ይግባኙን የተመለከተው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ካፀናው ወይም ይግባኙን ካልተቀበለው ይግባኝ ባዩ ለበላይ ፍ/ቤት በድጋሚ ይግባኝ የማለት መብት አይኖረውም፡፡ በአጠቃላይ በተለይ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች አንድ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ለበላይ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርበው እንዲታይላቸው የማድረግ መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሕገ መንግስታዊ መብት ለሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ ማቅረብን የሚያጠቃልል እንዳልሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡ይግባኝ ባዩ ያለው አማራጭ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈፅሟል የሚል እምነት ካለው ወደ ሰበር ሰሚው ፍ/ቤት ብቻ ማቅረብ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ሌላው ተከራካሪ ወገን ቅጣት አንሷል ብሎ የይግባኝ አቤቱታ ካቀረበ እና የበላይ ፍ/ቤት አቤቱታውን ተቀብሎ ቅጣቱን ከጨመረ ተቀጪው በዚሁ ውሣኔ ላይ ብቻ ለአንድ ጊዜ ወደ ቀጣዩ የበላይ ፍ/ቤት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የይግባኝ መብት አንድ እርከን ብቻ ነው የሚለው የይግባኝ ሥርዓት ቁጥሩ ላይበተለያዩ ክልሎች የሚለያይ ቢሆንም አሰራሩ በተመለከተ ተመሳሳይ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ዳኛ ፀጋይ አስማማው ይናገራሉ፡፡
ሁለተኛ ይግባኝ ማለት የሚፈቀደው ውሣኔውን ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ካሻሻለው ብቻ እንደሆነ ነው የሚገልፁት ፡፡አዋጅ ቁጥር 25/88 የሥር ፍ/ቤት በሰጠው ውሣኔ ወደሚቀጥለው ፍ/ቤት ይግባኝ ከተባለበት ያ ፍ/ቤት የሥር ፍ/ቤት ውሣኔን ካሻሻለ ሁለተኛ ይግባኝ ማለትን እንደሚፈቅድ ይጠቅሳሉ ፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር ሲታይ ሕጉ ግልፅነት የሚጎድለው ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ የሚሉ ባለጉዳዮች ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሣኔውን ያሻሻለው ይግባኝ ባዩን በሚጠቅም መልኩ ከሆነ ይኸ ሰው እንደገና ይግባኝ የማለት መብት ሊኖረው እንደማይገባው ነው፡፡
ይግባኝ እና የዳኞች ተጠያቂነት
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 78 ነፃ ፍ/ቤት መቋቋሙንና አንቀጽ 79 ደግሞ ዳኞች ሥራቸውን ያለምንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት ማከናወን እንዳለባቸው ይገልፃል፡፡ እንደ ዳኛ ሽመክት አሰፋ አገላለፅ ለተቋሙና ለዳኞች የተሰጠው ነፃነት አለጠያቂ እንዳሻቸው እንዲሆኑ ሳይሆን ከማንም ጣልቃ ገብነት ነፃና ገለልተኛ ሆነው በሕግና በሕግ ብቻ ተገዝተው ትክክለኛና አግባብነት ያለው ዳኝነት እንዲሰጡ ለማስቻል ያለመ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነፃ ስለተባለ በቻ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የዳኝነት አካሉ ያለበትን ተጠያቂነት ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ ከይግባኝና ከይግባኝ ስርዓት ጋር የተያያዘ መሆኑን በአፅንኦት ያሰምሩበታል፡፡ ጉዳዩን በመጀመሪያ ያየው ፍ/ቤት የሰጠውን ፍርድ ወይም ውሳኔ ተመልሶ ማንም የማያያው ከሆነ ዳኛው ሆነ ችሎቱ እንደወደዱ ይሰራሉ ማለት ነው ራሳቸውንም አያርሙም፡፡ ሂደቱ በይግባኝ እንዲታይ የማይፈቅድ ከሆነ ክፍተት ይኖራል፡፡ ስህተቶች ሳይታረሙ ያልፋሉ፡፡ የዚህ ውጤት ፍትህ በማንገስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ ስርዓት ዳግም የሚመረመርና የሚታይ ከሆነ ደግሞ የሥር ፍ/ቤት የተሳሳተ ውሳኔእየተሻረና እየተሻሻለ እንዲሄድ ስለሚያደርግ የተጠያቂነት መንፈስ እንዲሰርፅ ያግዛል፡፡ የስር ፍ/ቤት ለወደፊት ማረም ያለበትን ያርማል ያስተካክላል፡፡
የዳኝነት አካሉ የተጠያቂነት አሰራር ከዚህም ያለፈ እንደሆነ ነው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ አቶ ሽመክት የሚገልፁት፡፡ “በሕግና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚያስጠይቅ ጉዳይ ካለም ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ያ እንዳለ ሆኖ ግን ዳኝነትን ዳኛው ራሱን እያረመ እንዲሄድ ማድረግ የተጠያቂነት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ የዲሲኘሊን ወይም የሥነ-ምግባር ችግር ሲያጋጥም በሌላ መንገድ ተጠያቂ መሆን እንዳለ ሆኖ በይግባኝ በኩል ሥራው ተጠያቂነት ያለው ሥራ እንጂ ነፃ ነው ስለተባለ እንደተፈለገ የሚሰራ ያለመሆኑ ያመለክታል፡፡” በዚህ ጉዳይ ዳኛ ፀጋይም ሓሳቡን ይጋራሉ፡፡የይግባኝ ስርዓት ውሳኔዎች ጥራት እንዲኖራቸውና የስር ፍ/ቤቶች በጥንቃቄ እንዲሰሩ ያደርጋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

Comments

Be the first to add a comment