ጋብቻን ለመፈጸም በቅድሚያ መሞላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች
በሀገራችን የቤተሰብ ሕግ ሶስት ዓይነት የጋብቻ ስርዓቶች እንዳሉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ እነዚህም፡- 1. በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸም ጋብቻ፣
2. በሀይማኖት ስርዓት መሠረት የሚፈጸም ጋብቻ እና
3. በባህል ስርዓት መሠረት የሚፈጸም ጋብቻ ናቸው፡፡
ጋብቻ ቢፈጸምም ሶስቱም ዓይነት የጋብቻ መፈጸሚያ ስርዓቶች በቅድሚያ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መሰረታዊ የሆኑ ናቸው፡፡
1. ፈቃደኝነት (Consent)
የሚጸና ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነፃና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ እንደሆነ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 6 ላይ ተገልጿል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 34(2) ላይ “ጋብቻ በተጋቢዎቹ ነፃና ሙሉ ፈቃድ ላይ ብቻ ይመሰረታል” ይላል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም አይነት ጋብቻ አፈፃፀም ስርዓት ጋብቻ ቢፈጸምም የተጋቢዎቹ ነፃ እና ሙሉ ፈቃደኝነት አስፈላጊ ነው፡፡
2. እድሜ (Age)
ጋብቻ ራሱን የቻለ ኃላፊነት የሚያስከትል በመሆኑ ወደ ጋብቻው የሚቀላቀሉት ተጋቢዎች ይህን ኃላፊነት መቀበል የሚችሉ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጤና አንጻርም ወደ ጋብቻ የሚገቡ ሰዎች እድሜያቸው ብቁ መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ተጋቢቹ ለጋብቻው ፈቃዳቸውን በነፃ መስጠት መቻል አለባቸው፡፡ በዚህ በተሻሻለው ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 7(1) ላይ ወንዱም ሆነ ሴቷ አስራ ስምንት አመት ሳይሞላቸው ጋብቻ መፈጸም እንደማይችሉ ይገልፃል፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ ይህ እድሜ ሳይሞላ በፍትህ ሚኒስቴሩ ከመደበኛ እድሜ ሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ በመቀነስ እንዲጋቡ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ብቻ ነው፡፡
3. ዝምድና (Affinity and Consagunity)
ከህብረተሰቡ ሞራልና ከጤና ምክንያት የተነሳ ተጋቢዎች የቅርብ ዘመድ (የስጋም ሆነ የጋብቻ ዘመድ) መሆን እንደሌለባቸው እሙን ነው፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 8 እና 9 ላይ ክልከላው በግልጽ የተቀመጠ ነው፡፡


4. በጋብቻ ላይ ጋብቻ (Bigamy)
የፀና ጋብቻ ያለው አንድ ሰው ይህ ጋብቻ ጸንቶ እያለ ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማይችል በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 11 ክልከላ ተጥሎበታል፡፡
5. በብቸኝት ለመኖር የተወሰነ ጊዜ (Period of Widowhood)
ይሄኛው ክልከላ ወይም ቅድመ ሁኔታ ከላይ ካሉት አራት ቅድመ ሁኔታዎች ለየት ባለ መልኩ በሴቶች ላይ ብቻ የተጣለ ነው፡፡ አንዲት ሴት አስቀድሞ የነበራት ጋብቻ ከቀረ በኋላ አንድ መቶ ሰማኒያ ቀን ካላለፈ በቀር ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማትችል ክልከላ ተጥሎባታል፡፡ ነገር ግን ይህ አንድ መቶ ሰማኒያ ቀን ሳይደርስ የወለደች እንደሆን ወይም ጋብቻ የምትፈጽመው ከቀድሞ ባለቤቷ ጋር ከሆነ ወይም እርጉዝ አለመሆኗ በህክምና ከተረጋገጠ ወይም ይህን ጊዜ እንዳትጠብቅ በፍ/ቤት የተወሰነ እንደሆነ ይህን ጊዜ ሳትጠብቅ ጋብቻ ልትፈጽም እንደምትችል በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 16 (2) ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህ ክልከላ በመሰረታዊነት የተቀመጠው የህፃናትን መብት ለመጠበቅ ነው፡፡ ህፃናት ወላጆቻቸውን የማወቅና ከወላጆቻቸው እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕገ-መንግስታችንና አለማቀፍ ስምምነቶች ላይ የተቀመጡ እና የተረጋገጠ መብታቸው ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ክልከላ በማድረግ የሕፃናትን መብት ለማስከበር የወላጆቻቸው ማንነት ላይ አከራካሪ ሁኔታ እንዳይፈጠር ነው፡፡

ቸር ሰንብቱ
ፌናን ተጊበሉ
ጥር 14/2013 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment