የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
በስታቲስቲክስ
ተግባር የተሰበሰበ የግለሰብ መረጃ በማንኛውም ተቋማት ዘንድ ለምርመራ፣ ለደህንነት፣ ለሕግ ወይም ለአስተዳደራዊ ውሳኔዎች እንዳይውል የሚከለክል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ።
ለልማት ዕቅድና ለፖሊሲ ቀረጻ የሚውሉ መረጃዎችን በዘመናዊ መንገድ ለማመንጨት ያስችላል የተባለ የስታቲስቲክስ አዋጅ ተዘጋጅቶ የሚኒስትሮች ምክርቤት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል።
አዲሱ አዋጅ በዋናነት ያስፈለገው የሀገሪቱን የልማት ዕቅዶች፣ የፖሊሲ ቀረጻዎችና የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሞችን በተሟላ መረጃ ለመደገፍ ሲሆን፤ከዚህ ባለፈም ከሃያ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ነባሩ ሕግ እንደ ቢግ ዳታ (big data)፣ ጂኦስፓሻልና ዲጂታል የመሳሰሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና የመረጃ ምንጮችን ለማስተናገድ አቅም ማጣቱ ለለውጡ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል ተቋማዊ ተጠያቂነትን፣ ግልጽነትንና ሙያዊ ነፃነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
ይህም በብሔራዊ ደረጃ የሚታዩ የመረጃ ድግግሞሾችንና እርስ በእርስ የሚጋጩ ዳታዎችን በማስቀረት፣ የኢትዮጵያን የመረጃ አያያዝ ከተባበሩት መንግሥታትና ከአፍሪካ የስታቲስቲክስ ቻርተር መርሖዎች ጋር ለማጣጣም ያለመ ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የተሰኘውን ተቋም በድጋሚ በማቋቋም፣ ተቋሙ የራሱ ቦርድና የሥራ አመራር እንዲኖረው ያደርጋል።
ይህ አዲስ መዋቅር ተቋሙ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ ሙያዊና ሳይንሳዊ ግኝቶችን ብቻ መሠረት አድርጎ እንዲሠራ የሚያስችል መሆኑ በረቂቁ ላይ ተመላክቷል።
ተቋሙ ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ ቢሆንም፣ በቴክኒካዊና በስታቲስቲካዊ ሥራዎቹ ላይ ግን ሙሉ ነፃነት እንደሚኖረው ተደንግጓል።
በዚህ አዋጅ የስታቲስቲክስ ትርጉም ሰፋ ባለ መልኩ ቀርቧል ከዚህ ቀደም ከሚታወቁት የሕዝብ ቆጠራና የናሙና ጥናቶች በተጨማሪ፣ አዲሱ ረቂቅ እንደ "ቢግ ዳታ" (Big Data)፣ የሳተላይት መረጃዎች (Geospatial Data)፣ የዲጂታል ምንጮችና በሴንሰር የተደገፉ መረጃዎችን እንደ ስታቲስቲክስ ምንጭነት ዕውቅና ሰጥቷቸዋል።
"ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ሥርዓት" (National Statistical System) በሚል የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የሚሰበስቧቸው መረጃዎች ተቀራራቢና ወጥ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም የሥራ ድግግሞሽን ለማስቀረት የተቀናጀ አሠራር እንዲዘረጋ ያዝዛል።
ማንኛውም ተቋም የሚያመነጨው መረጃ በኢትዮጵያ የዳታ ጥራት ቁጥጥር ማዕቀፍ ውስጥ ማለፍ እንደሚኖርበትም ተደንግጓል።
የዜጎች የግል መረጃ ምስጢራዊነት አጠባበቅም በተመለከተም በስታቲስቲክስ ተግባር የተገኘ የግለሰብ ዳታ ለስታቲስቲክስ ዓላማ ብቻ የሚያገለግል ሲሆን፣ በማንኛውም ሀገራዊ ወይም የዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ለምርመራ፣ ለደህንነት፣ ለሕግ ወይም ለአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ሊውል እንደማይችል ረቂቁ በግልጽ ያሳስባል።
የግለሰቦችን መለያዎች የያዙ ሁሉም የዳታ መሰብሰቢያ ቅጾች ለስታቲስቲክስ ዓላማዎች አስፈላጊነታቸው እንዳበቃ ወዲያውኑ መወገድ አለባቸው፡፡
የግለሰቦችን ማንነት የሚገልጽ መረጃ አሳልፎ መስጠት በረቂቁ መሰረት በወንጀል የሚያስጠይቅ ነው።
ረቂቅ አዋጁ በመረጃ አሰባሰብ ሂደት ላይ ለሚታዩ መሰናክሎች የቅጣት ድንጋጌዎችን ያስቀመጠ ሲሆን ማንኛውም መረጃ እንዲሰጥ የተጠየቀ አካል የተሳሳተ መረጃ ቢሰጥ ወይም ለመተባበር ፈቃደኛ ባይሆን በወንጀል ሕግ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ ግንቦት 18 የተካሄደው 55ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ፣ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱን መገለጹ ይታወሳል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ/ም
Comments
Be the first to add a comment