የደቡብ ሱዳን መንግሥት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጁባ ከተማ ለሚያከናውነው  የዘመናዊ ቤቶች ግንባታ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገለጸ

ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት ያደረገ ሲሆን፣ የህንጻ ግንባታ ሳይቶች መረጣ እና ተያያዥ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች አፈጻጸምም በግዛቱ የኮንስትራክሽን እና ቤቶች ኮርፖሬሽን በቀረበየጥናት  ሪፖርት  አማካኝነት  በዝርዝር  ተገምግሟል።

​ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባር የሚያስገባው ይኸው አዲስ ውል በጁባ ከተማ ተፈርሟል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በዶክተር ረሻድ ከማል እና በደቡብ ሱዳን ሴንተራል ኢኳቶሪያል ግዛት አስተዳዳሪ በክቡር ኢማኑኤል አድል ስምምነቱን ፈርመዋል፡።

በዚህም መሠረት ኮርፖሬሽኑ በጁባ ከተማ ዘመናዊ የንግድና የመኖሪያ ሕንጻዎችን የሚገነባ ይሆናል።

​ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ረሻድ ከማል ከደቡብ ሱዳን መንግስት ልዩ መልዕክተኛ ከክብርት አዱት ኪር ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር ደሊል ከድር እና በደቡብ ሱዳን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩት ታዋቂው ባለሀብት ዶክተር አይሸሽም ተካ ተገኝተዋል።

​በመድረኩ ላይ ክብርት አዱት ኪር ኮርፖሬሽኑ በጁባ ከተማ ለሚያካሂደው የቤት ልማት ፕሮግራም የደቡብ ሱዳን ፌዴራል መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ይህ የቤት ግንባታ መጀመር በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን ሙሉ እምነት በመግለጽ፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት ያለውን  ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የፌቤኮ ​ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዶክተር ረሻድ ከማል በበኩላቸው፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በደቡብ ሱዳን የቤት ልማት ዘርፍ የተሰማራው የጋራ ተጠቃሚነትን፣ አብሮነትን እና ወንድማማችነትን መርህ አድርጎ መሆኑን ገልጸው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቆ ግንባታው በይፋ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ረሻድ ከማል እና በርሳቸው የሚመራው የሥራ ልዑካን ቡድን ለአራት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ጉብኝት አጠናቆ  ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡

@etconp

Comments

Be the first to add a comment