በኢትዮጵያ የሊፍት ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈረመ

በኢትዮጵያ በአሳንሰር ወይም በሊፍት ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚታየውን የአገልግሎት እና የጥገና ክፍተት ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር የሚያስችል የጋራ ኢንቨስትመንት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት ተፈርሟል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት ሀገር በቀሉ የቴክኖሎጂ ድርጅት ሞናጎ ኢሊቬተር እና የቱርኩ ኬ. አር. ሲ ኢሊቬተር ኩባንያ ናቸው።

ላለፉት አምስት ዓመታት አብረው ሲሰሩ የቆዩት ሞናጎ እና ኬ. አር .ሲ ኢሊቬተር ኩባንያዎች፤ አሁን ላይ ግንኙነታቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር በኢትዮጵያ የሊፍት ማምረቻ ፋብሪካ በጋራ ለመገንባት ተስማምተዋል።

የሞናጎ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋሁን ኢሳያስ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ በሀገሪቱ የሊፍት ቴክኖሎጂ ላይ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

በተለይም ቀደም ሲል በግዢ እና በጨረታ ሂደት የሚገጠሙ ሊፍቶች ከሽያጭ በኋላ በቂ የጥገና አገልግሎት እና የስፔር ፓርት አቅርቦት ባለማግኘታቸው ምክንያት ስራ የማቆም ችግር ይገጥማቸው እንደነበር ጠቁመዋል።

አዲሱ አጋርነት ይህንን ክፍተት በመሙላት የቅርብ ክትትል፣ የጥገና እና የስፔር ፓርት አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረት የመንግስት የመሬት አቅርቦት ድጋፍን በመጠቀም የሚገነባው ይህ ፋብሪካ፤ የቱርኩን የላቀ ማሽነሪ እና ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባ ይሆናል።

ከዚህም በተጨማሪ ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችን በመስጠት ዘላቂ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ ታቅዷል።

ይህ የጋራ ኢንቨስትመንት ምርቱን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት ሲጀምር፤ የውጭ ምንዛሬን ለማዳን፣በህንፃዎች ላይ የሚገጥሙ የአሳንሰር ስራ ማቆም ችግሮችን ለማስወገድ እና በዘርፉ አዲስ የኢንዱስትሪ ደረጃን ለመፍጠር ሚና እንደሚጫወት ተመልክቷል።

Via Ethio FM 107.8

@etconp

Comments

Be the first to add a comment