የፍርድ ቤቶች ስልጣን
የፍርድ ቤቶች አንድን ክርክር አይተዉ አከራክረዉ ለመወሰን ስልጣን አላቸዉ የሚባለዉ በህግ ተወስኖ ሲሰጣቸዉ ነዉ፡፡የፍርድ ቤቶችን ስልጣን ለይተዉ ከቀረቡ ህጎች መካከልም የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013፣ የተሻሻለዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ቁጥር 361/1995፣ የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ስነ-ስርአት ሕግ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ የፍርድ ቤቶች ስልጣንም ሲባል ከማህበራዊ ፍርድቤት ተነስቶ እስከ ፌደራል ፍርድ ቤቶች ያሉትን ያካትታል፡፡
የአንድ ፍርድ ቤት ስልጣንም ሊወሰን የሚችለዉ፡-
1. በሚከራከሩበት ንብረት የዋጋ መጠን
2. በተከራካሪ ወገኖች ማንነት 
3. የሚከራከሩበት ንብረት የሚገኝበት ቦታ
4. ተከራካሪ ወገኖች የሚገኙበት ቦታ
5. በዉል ጉዳይ ከሆነ ዉሉ የተፈረመበት ቦታ፣ ሊፈጸምበት የታሰበዉ ቦታ በመሳሰሉት
6. በሚከራከሩበት ጉዳይ የግዝፈት መጠን እንዲሁም በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ ይወሰናል፡፡
የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ስልጣንን በተመለከተ
በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ላይ ስንመለከት አንቀጽ 4(16) ላይ የወንጀል ጉዳዮችን የሚያይበት ስልጣኑ የተለየ ሲሆን በፍትሐብሔር ጉዳዮች ዙሪያ አንቀጽ 5(ደ) ስር ተዘርዝረዉ ይገኛሉ፡፡
የተሻሻለዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ቁጥር 361/1995 በሌላ መልኩ ደግሞ በአንቀጽ 41 ላይ የፍትሐብሔር እና ወንጀል ስልጣናቸዉን አስቀምጧል
ይህን ካልን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሉት ፍርድ ቤቶች  የመጀመሪያ ደረጃ እና  ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ናቸዉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ለከተማዉ የተሰጠዉን የፍትሐብሔር እና የወንጀል ጉዳዮች አጠቃሎ የሚያይ ሲሆን የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ዉሳኔ ያገኙ ጉዳዮችን በይግባኝ ያያል።  ነገር ግን በይግባኝ ፍርድ ቤቱ በተሰጠዉ ዉሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን በአገሪቱ ባሉ  ፍርድ ቤቶች የተሰጠን የመጨረሻ ዉሳኔ የማየት ስልጣን ለተሰጠዉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ማቅረብ ይቻላል። በመጨረሻም ህገ መንግስታዊ ዉሳኔ ለሚያስፈልጋቸዉ ጉዳዮች የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፍትህ ስርዓቱን የመጨረሻ ዉሳኔ ይሰጣል።
ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስንመጣ  ከከተማ ፍርድ ቤቶች የሚለያቸዉ 3 እርከን ስላላቸዉ ነው። የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ፣ ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ናቸዉ። የፍርድ ስልጣናቸዉም በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ላይ ተለይቶ ተቀምጥዋል። አንድ ተከራካሪ ወገንም የመጀመሪ ደረጃ ፍርድ ቤት ክርክሩን አቅርቦ ዳኝነት የጠየቀበት ጉዳይ ዉድቅ ቢደረግበት የይግባኝ ቅሬታዉን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚያቀርብ ሲሆን የመጀመሪያው ዉሳኔ ከጸና ጉዳዩን ለሰበር ችሎት አቅርቦ የህግ ስህተት ካለ ከማሳረም ዉጪ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አቅርቦ ለሁለተኛ ግዜ ይግባኝ ማቅረብ አይችልም። ይህም ማለት አንድ ጉዳይ ከአንድ ግዜ በላይ ይግባኝ ሊባልበት አይችልም። የከፍተኛ ፍርድ ቤትም በመጀመሪያ ፍቅደ ስልጣኑ ያየዉን ክርክር ይግባኝ ሊባልበት የሚችለዉ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሆናል።
ዉበአለም መስፍን የቦ/ክ/ከ/ፍ/ጽ/ቤት/የህ/ስ/ም/መ ዳይሬክቶሬት ዐ/ህግ

Comments

Be the first to add a comment