👉በ3ዲ ቴክኖሎጂ የታተሙት የኮሎምቢያ የማኀበራዊ መኖሪያ ቤቶች ለዘርፉ አዲስ ተስፋ ሰንቀዋል

በደቡብ አሜሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ዲ (3D) የህትመት ቴክኖሎጂ የተገነቡ የማህበራዊ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በኮሎምቢያ በስኬት ተጠናቀቀ፤

ይህ ታሪካዊ ክንውን በሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል በአንቲዮኪያ ግዛት ስር በምትገኘው ላ ዩኒየን ከተማ የተከናወነ ሲሆን፣ ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ለቤት እጥረት አዲስና ፈጣን መፍትሄ እንደሚሆን ታምኖበታል፤
ďťż
ግንባታው የተከናወነው "ፈንዳሲዮን በርታ ማርቲኔዝ" ለተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ሲሆን፣ የኮሎምቢያው የሲሚንቶ ግዙፍ ኩባንያ ሴሜንቶስ አርጎስ (Cementos Argos) ከዴንማርኩ የ3ዲ ፕሪንተር አምራች ኮቦድ (Cobod) ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱን አሳክተዋል። ለግንባታውም ቦድ-2 (Bod2) የተባለውን ዘመናዊ የህትመት ማሽን ጥቅም ላይ አውለዋል፤

እነዚህ ባለ አንድ ፎቅ ቤቶች እያንዳንዳቸው 63 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ሲሆን፣ ሁለት መኝታ ቤቶች፣ ሳሎን፣ ኩሽና፣ መታጠቢያ ቤት፣ የልብስ ማጠቢያ ቦታና በረንዳ ያካተቱ ናቸው። ቤቶቹ 2.2 ሜትር ከፍታ ያላቸው የታተሙ ግድግዳዎችና ከእንጨት የተሠራ ጣሪያ ያላቸው በመሆኑ ዘመናዊነትንና ምቾትን አጣምረው የያዙ ናቸው፤

የቴክኖሎጂው ዋነኛ መገለጫ የሆነው ፍጥነት በዚህ ፕሮጀክት ላይ በተግባር የታየ ሲሆን፣ ሁለቱም ቤቶች በድምሩ በ16 የህትመት ሰዓታት ውስጥ በሶስት ቀናት ብቻ ተጠናቀዋል። ይህም ከተለመደው የግንባታ ዘዴ ጋር ሲነፃፀር በ30 በመቶ የፈጠነ መሆኑንና ግንባታን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ያለውን አቅም አሳይቷል፤

ከጊዜ ቁጠባው በተጨማሪ ቴክኖሎጂው በኢኮኖሚ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው በተደረገው ምልከታ ተረጋግጧል። በግንባታው ወቅት የሚባክኑ ግብዓቶችን ከ15 እስከ 30 በመቶ መቀነስ የተቻለ ሲሆን፣ የቁሳቁስ ወጪንም በ20 በመቶ ያህል ዝቅ እንዲል በማድረግ የማህበራዊ ቤቶችን ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲኖራቸው አድርጓል፤

ለህትመቱ የዋለው የሲሚንቶ ውህድ 99 በመቶ በአካባቢው ከሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች የተዘጋጀ መሆኑ ሌላው የፕሮጀክቱ ስኬት ነው። የቤቶቹ ግድግዳዎች ከ35 ሜጋ ፓስካል (MPa) በላይ የመጫን ጥንካሬ ያላቸው በመሆኑ፣ የአካባቢውን የመሬት መንቀጥቀጥ መቋቋም የሚችሉና የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፤

በውህዱ ውስጥ የተካተቱት ልዩ ቃጫዎችና ኬሚካላዊ ቅመሞች ግድግዳዎቹ በአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት እንዳይሰነጣጠቁ የመከላከል ብቃት አላቸው፤

በተጨማሪም ግድግዳዎቹ በመካከላቸው የአየር ክፍተት እንዲኖራቸው ተደርገው የታተሙ በመሆኑ፣ በቤት ውስጥ ያለውን ሙቀትና ቅዝቃዜ የመቆጣጠር (Thermal insulation) ብቃት እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል፤

የ3ዲ ፕሪንተር ማሽኑ በአምስት ትናንሽ የጭነት መኪናዎች ተጭኖ አስቸጋሪ በሆነ ተራራማ መልክዓ ምድርና ዝናባማ የአየር ሁኔታ ውስጥ ተጓጉዞ ግንባታው ወዳለበት ቦታ ደርሷል። ይህም ቴክኖሎጂው መሠረተ ልማት ባልተሟላላቸውና ርቀው ለሚገኙ አካባቢዎች ግንባታን ለማካሄድ ያለውን አመቺነት በተግባር ያረጋገጠ ክስተት ሆኗል፤

ማሽኑን ለማንቀሳቀስ ከ3 እስከ 4 የሚደርሱ ሰዎች ብቻ የሚያስፈልጉ በመሆኑ፣ በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። አነስተኛ መነሻ ካፒታል ያላቸው ድርጅቶችም ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጥራት ያላቸው ቤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋና በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲገነቡ ዕድል እንደሚሰጥ ባለሙያዎች ገልጸዋል፤

ሴሜንቶስ አርጎስ በቀጣይ 20 የማህበራዊ መኖሪያ ቤቶችን በአንድ ላይ የመገንባት ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ ግድግዳዎችን ከግንባታ ቦታ ውጪ አትሞ በማምጣት የመገጣጠም ዘዴን ለመተግበር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፤

ይህ እንቅስቃሴ የቴክኖሎጂውን ተደራሽነት ይበልጥ እንደሚያሰፋውና በኮሎምቢያ የገጠር አካባቢዎች ያለውን የቤት ፍላጎት እንደሚቀንስ ይጠበቃል።

@etconp

Comments

Be the first to add a comment