ጤና ይስጥልኝ!!
በየትኛውም የሰው ልጆች ዕንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች ልዩነት መኖሩ ተፈጥሯዊ መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ልዩነቱን ለጉዳት ሳይሆን ለጥቅም በሚውልበት መልኩ እውቅና መስጠት የጤናማና ስልጡን ማህበረሰብ ምልክት በመሆኑ የእዚሁ አስተሳሰብ ክፍል የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2011 በአምስተኛ ክፍሉ ከአንቀጽ 48 እስከ አንቀጽ 50 ባሉት አንቀጾች ልዩ ድጋፍ በቅጥር፣ በምደባ፣ በዝውውር፣ በደረጃ እድገት፣ በቢሮ ምደባ፣ በግብዓት ማሟላት፣ በረጅምና በአጭር የትምህርት እድሎች፣ እና በመሳሰሉት ለእነዚህ ሰራተኞች ሊደረጉ ስለሚገባቸው ልዩ ድጋፎች በግልጽ የደነገገውን ከዚህ እንደሚከተለው እንካቹህ!!
ለሴት ሰራተኞች የሚጠበቁ የስራ ሁኔታዎች
1. ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ሴት የመንግስት ሰራተኞች ለማብቃትና በውሳኔ ሰጪ የስራ ቦታዎች ላይ እንዲመደቡ ለማድረግ የሚያስችሉ የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃዎች መውሰድ አለበት፡፡
2.ሴቶች በቅጥር በደረጃ እድገት በዝውውር በድልድል በትምህርትና ስልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡
3.ነፍሰ ጡር የሆነችን የመንግስት ሰራተኛ በቅጥር ወይም በደረጃ እድገት ከተመደበችበት የስራ መደብ ወደ ሌላ የስራ መደብ መድቦ ማሰራት የተከለከለ ነው ሆኖም ለራሷ ጤንነት ወይም ለጽንሱ አደገኛ መሆኑ በህክምና ማስረጃ ሲረጋገጥ ተስማሚ ወደ ሆነ የስራ መደብ ወይም የስራ ቦታ ተመድባ እንድትሰራ መደረግ አለበት፡፡
3.ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ሴት የመንግስት ሰራተኛ ነፍሰጡር በሆነችበት ጊዜና ከወለደችበት ቀን ጀምሮ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 87 መሰረት በሚደረገው የሰራተኛ ቅነሳ ከስራ ሊያሰናብታት አይችልም፡፡
4.ማንኛዋም ሴት የመንግስት ሰራተኛ አንድ አመት ያልሞላውን ህጻን ልጇን ለማሳከም በህክምና ማስረጃ ለተረጋገጠ ጊዜ ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣታል በተለያየ ምክንያት እናት ባትኖር ይህ ፈቃድ የመንግስት ሰራተኛ ለሆነ ልጁ አባት ወይም አሳዳጊ ይሰጣል፡፡
5.ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ሴት የመንግስት ሰራተኞች ህጻናት ልጆቻቸውን የሚያጠቡበትና ህጻናቱን የሚንከባከቡበት ህጻናት ማቆያ ማቋቋም አለበት፡፡
ለአካል ጉዳተኞች የሚጠበቁ የስራ ሁኔታዎች
1.አካል ጉዳተኞች በቅጥር በደረጃ እድገት በዝውውር በድልድል በትምህርትና ስልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡
2.ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የስራ አካባቢው ለአካል ጉዳተኛ ሰራተኞች ምቹ መሆኑን ማረጋገጥ ለስራ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ማሟላትና ስለአጠቃቀማቸው አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ አለበት፡፡
3.ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ረዳት ለሚያስፈልገው የአካል ጉዳተኛ የሆነ የመንግስት ሰራተኛ ተገቢውን ድጋፍ ሊሰጥ የሚችል ረዳት እንዲመደብለት የማድረግ ሃላፊነት አለበት፡፡
4.በሌሎች ሕጎች በአዋጅ ቁጥር 568/2000፣ በአለማቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ለአካል ጉዳተኞች የተሰጡ መብቶች ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡
አነስተኛ ብሔራዊ ተዋጽኦ ስላላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚጠበቁ የስራ ሁኔታዎች
1.በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚፈጸም የሰራተኛ ስምሪት የብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፡፡
2.በመንግስት መስሪያ ቤቱ ውስጥ አነስተኛ ብሔራዊ ተዋጽኦ ያላቸው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቅጥር በደረጃ እድገት በዝውውር በድልድል በትምህርትና ስልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡
ሲሳይ ሰማኝ (መስከረም 15/2014 ዓ.ም)

Comments

Be the first to add a comment