የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
በቦሌ ክፍለከተማ አስተዳደር
የአቃቤህግ ጽፈትቤት የህግ ስርጸት ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
በኢፌድሪ የወንጀል ህግ
ስለሚስጢር መግለጽ የተደነገገውን በማስመልከት
የተዘጋጀየቴሌግራም መልዕክት-
ነሐሴ 2013
መግቢያ-
ውድ ተከታታዮቻችን በቅርቡ በኢፌድሪ የሐገር መከላከያ ሰራዊት የደቡብ እዝ ተቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሚስጥር በማውጣትና ሙያዊነትን በጣሰ ሁኔታ በመንቀሳቀስ በሀገሪቱና በሰራዊቱ ላይ ባደረሱት ጉዳት መሰረት 10ሰዎችን ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አንቀጾች መሰረት ቀጥቷቸዋል፡፡ በዚህ መልዕክት በወንጀል ህጋችን በሙያ፣ በሀላፊነት፣ በሽምግልና ባጠቃላይ በማንኛውም መስፈርት ታምነን ወይም የስራ ባህሪያችን ሆኖ ያወቅነውን ሚስጢር ባለመጠበቃችን ሊገጥመን ስለሚችለው ቅጣት ግንዛቤ ለመፍጠር በወንጀል ህጋችን የተደነገገውን እንደሚከተለው አቅርበናል
መልካም ምንባብ፡፡
የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከት ምስጢርን መግለፅ
አንቀጽ 396 ወታደራዊ ምስጢርን መግለፅ
1. ማንኛውም ወታደር ወይም በመከላከያ ኃይል አገልግሎት ውስጥ የሚገኝ ሰው ክዳትንና ስለላን በሚመለከት ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች /አንቀጽ 248-252/ ውጭ፣ በሥራው ወይም በወታደራዊ ግዳጅ ምክንያት ያወቀው ሆኖ በጠባዩ ምስጢር የሆነውን ወይም ምስጢር ሆኖ እንዲጠበቅ የታዘዘውን ወይም ለሕዝብ እንዳይገለጽ የተከለከለውን መረጃ፣ ሰነድ ወይም ፍሬ ነገር የገለፀ ወይም ያስተላለፈ እንደሆነ፤
ሥራው ወይም ግዳጅ ከተፈፀመ በኋላ ቢሆንም እንኳን ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
2. ቅጣቱ ከአሥራ አምስት ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እሥራት የሚሆነው፡-
ሀ/ ወንጀሉ የሚመለከተው በምስጢር ኮድ /አሀዝ/ የተያዘ መረጃን ወይም ሰነድን እንደሆነ፣ ወይም አድራጊው ምስጢሩን እንዲጠብቅ በግልፅ አደራ የተጣለበት ወይም ምስጢሩን እንዳይገልፅ የመሐላ ቃሉን የሰጠበት እንደሆነ፤ ወይም
ለ/ ወንጀሉ ልዩ በሆነ ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሶ እንደሆነ፤
ነው፡፡
3 ወንጀሉ በቸልተኛነት ተፈጽሞ እንደሆነ ከዚህ በላይ በንዑስ አንቀጽ (1) ለተመለከተው ቀላል ወንጀል ቅጣቱ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ቀላል እሥራት ወይም መቀጮ፤ በንዑስ አንቀጽ (2) ለተመለከተው ከባድ ወንጀል ደግሞ ከሦስት ዓመት ያልበለጠ ቀላል እሥራት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 397 የሥራ ምስጢርን መግለፅ ነው፡፡
1 ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ /አንቀጽ 42/ በአንቀጽ 396 በተመለከተው ድንጋጌ በተገለፀው መሠረት ምስጢር ሆኖ ሊጠበቅ የሚገባውን እና በሥራው ምክንያት ያወቀውን ማናቸውንም ዓይነት ሰነድ፣ መረጃ ወይም ፍሬ ነገር ሥራውን ወይም ሹመቱን ከለቀቀ በኋላ ቢሆንም እንኳ የገለጸ እንደሆነ፤
በቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡
2 ጥፋተኛው የተለየ ምስጢር የመጠበቅ ግዴታ ወይም እምነት የተጣለበት ወይም ወንጀሉ በተለይ ከፍ ያለ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከአስር ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይሆናል፡፡
3 ወንጀሉ የተፈጸመው በቸልተኛነት ሲሆን ቅጣቱ በንዑስ አንቀጽ (1) ለተመለከተው ቀላል ወንጀል ከብር አንድ ሺህ የማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ቀላል እሥራት፤ በንዑስ አንቀጽ (2) ለተመለከተው ወንጀል ደግሞ ከሦስት ዓመት ያልበለጠ ቀላል እሥራት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 398 እንዲገለፅ የተፈቀደ ምስጢር
ለህዝብ ጥቅም ሲባል አግባብ ባለው የሲቪል፣ አስተዳደራዊ ወይም ወታደራዊ ባለሥልጣን የጽሁፍ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ በፍርድ ቤት ወይም ሥልጣን ባለው በማናቸውም ምርመራ በሚያደርግ ፍርድ ቤት ፊት የተደረገ የምስጢር መግለፅ አያስቀጣም፡፡
አንቀጽ 399 በሞያ ወይም በሥራ ምክንያት የታወቀ ምስጢርን መግለፅ
1 የማናቸውም እምነት አገልጋይ፣ የሕግ አማካሪ፣ ጠበቃ፣ ነገረ ፈጅ፣ የሽምግልና ዳኛ፣ አስታራቂ ሽማግሌ፣ ልዩ አዋቂ/ኤክስፐርት/፣ ነባሪ፣ አስተርጓሚ፣ ውል አዋዋይ፣ የግል ድርጅት ዳይሬከተር፣ የሥራ መሪ፣ ተቆጣጣሪ ወይም በፍትሐብሔር ወይም በንግድ ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ምስጢር መጠበቅ የሚገበው ማንኛውም ሠራተኛ፣ ሐኪም፣ የጥርስ ሐኪም፣ የመድሀኒት ቅመማ ባለሙያ /ፋርማሲስት/፣ አዋላጅ፣ ነርስ ወይም ሌላ ረዳት የህክምና ሠራተኛ ወይም ሌላ በሙየው ወይም በሥራው ምክንያት የተገለጠለትን ምስጢር በሙያ ሥራው ላይ ሳለም ሆነ ሥራውን ከለቀቀ በኋላ የገለጸ እንደሆነ፤
የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡
2 በሞያ ሥራ መለማመድ ትምህርት ምክንያት ሊያውቅ የቻለውን ምስጢር የገለጸ ተማሪ፣ በሙከራ ላይ ያለ ሠራተኛ ወይም ተለማማጅ ሠራተኛ በንዑስ አንቀጽ (1) በተመለከተው ቅጣት ይቀጣል፡፡
3 ምስጢር የመግለፁ ወንጀል የተፈጸመው በቸልተኛነት እንደሆነ፤ የግል አቤቱታ ሲቀርብ ቅጣቱ ከብር አንድ ሺህ የማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት የማይበልጥ ቀላል እሥራት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 400 እንዲገለፅ የተፈቀደ ምስጢር
1 ምስጢር መግለፅ የማያስቀጣው፡-
ሀ/ ምስጢሩ ሊጠበቅለት የሚገባው ሰው በግልፅ ፈቃድ ከሰጠ በኋላ እንደሆነ፤
ለ/ ምስጢሩን በያዘው ሰው አሳሳቢነት ወይም ጠያቂነት አግባብ ያለው የበላይ የሙያ ወይም የቁጥጥር አካል የጽሁፍ ፈቃድ ሰጥቶ እንደሆነ፤
ሐ/ በአንድ በተወሰነ ጉዳይ ላይ የተሰጠን ግልፅ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት በማድረግ ተገልጾ እንደሆነ፤ ወይም
መ/ ለሕዝባዊ ተግባር ሲባል በፍርድ ችሎት እንዲመሰክር ወይም ላንዱ ባለሥልጣን መግለጫ እንዲሰጥ የሕጉ ልዩ ድንጋጌ የሚፈቅድ ወይም የሚያዝዝ እንደሆነ፤
በሕግ፣ በፍርድ ቤት ወይም በሚመለከተው ባለሥልጣን ምስጢር እንዲገልጽ የታዘዘ ሰው የሚስጢር መጠበቅ ግዴታውን ምክንያት በማድረግ ምስጢሩን ለመግለጽ እንቢተኛ ለመሆን አይችልም፡፡
በማናቸውም ምክንያት ሀይማኖታዊ ኑዛዜ እንዲገለፅ ለማስገደድ አይቻልም፡፡
አንቀጽ 401 የሳይንስ፣ የኢንዱስትሪ ወይም የንግድ ምስጢርን መግለፅ
1 ማንም ሰው ባለቤቱን ወይም ባለይዞታውን ለመጉዳት ወይም ጥቅም ለማግኘትም ሆነ ለማስገኘት በማሰብ በሕግ ወይም በውጭ ወይም በሥራው ኃላፊነት ምክንያት ያለበትን ግዴታ በመጣስ በምስጢር መጠበቅ የሚገባውን ማናቸውንም የኢኮኖሚ፣ የሳይንስ፣ ወይም የቴክኖሎጂ ግንባታ ዘዴ ወይም መረጃ፤ የኢንዱስትሪን ወይም የንግድን፣ የሳይንስን /ሥነ ጥበብ/ ምስጢር ወይም በሥራ ላይ የሚውልበትን ጥበባዊ ዘዴ ሊገለፅለት ለማይገባ ሰው የገለፀ እንደሆነ፤
ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት እና ከአሥር ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
2 ለአገር መከላከያ ጠቃሚ የሆነ የሳይንስ ወይም የስነጥበብ ምስጢር የተገለጸ እንደሆነ፤ በአንቀጽ 396 የተመለከተው ልዩ ድንጋጌ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
ሲሳይ ሰማኝ
ቸር ይግጠመን፡፡ ነሓሴ 28/12/2013 ዓ.ም
Comments
Be the first to add a comment