ስለንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ሕግ (ክፍል አንድ)
መግቢያ
ሀገራት ከሚከተሉት የኢኮኖሚ ሥርዓት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ወይም የዕዝ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ሁለቱንም የገበያ ኢኮኖሚ ባማከለ መልኩ የቅይጥ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትም ተጠቃሽ እንደሆነ ከተለያዩ ፅሁፎች መረዳት ይቻላል፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የንግዱን ህብረተሰብ ከፀረውድድር እና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት እንዲሁም ሸማቹን ከሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች የሚከላከል ሥርዓት መዘርጋት እና ለነፃ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ሥርዓት ማስፈን አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴዎች ማደግን ተከትሎ የሸማቾችን ጤንነትና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን መስፋፋት ለመግታት እንዲቻልና ተጠቃሚዎች ላወጡት ዋጋ ተመጣጣኝ የሆኑ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ታውጇል፡፡ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃን ስናስብ ነጋዴዎች እና ሸማቾች የገበያው ተዋንያን በመሆናቸው በዋናነት በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት ሊኖራቸው የሚገባ መብትና ግዴታዎቻቸውን በቅጡ ሊያውቁት ይገባል፡፡
ስለ ነፃ ገበያ ምንነት
ዓለማችን የምትመራባቸው ሶስት የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ሲኖሩ አነሱም፡- የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ፣ የዕዝ ገበያ ኢኮኖሚና የቅይጥ ገበያ ኢኮኖሚ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት ማለት ገበያው ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት እራሱን በራሱ የሚመራበት ስርዓት ማለትም ነጋዴዎች መንግስት በሚያወጣላቸው ዕቅድና መመሪያ ሳይሆን በተጨባጭ በገበያ ላይ ባለ ፍላጎትና አቅርቦት መሰረት መስራት የሚያስችላቸው ስርዓት ነው፡፡ የእዝ ገበያ የኮኖሚ ስርዓት የሚባለው ሀገራችን በደርግ ዘመነ መንግስት ትከተለው የነበረ የኢኮኖሚ ስርዓት ሆኖ ገበያው የሚመራው በፍላጎትና አቅርቦት ኃይሎች ባለ ነፃ መስተጋብር ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ኖሮበት የሚመራ የገበያ ስርዓት ነው፡፡ የቅይጥ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት የሚባለው ደግሞ የነፃ ገበያና የዕዝ ኢኮኖሚ የገበያ ስርዓቶች ድብልቅ ሆኖ ሁለቱም አካላት የየራሳቸው ሚና መጫወት የሚያስችል የገበያ ምህዳር ሲኖር ማለት ነው፡፡
ከአዋጁ መግቢያ መገንዘብ እንደሚቻለው ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትመራው በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት ነው፡፡ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት ትከተላለች ማለት ግን የንግዱን ዘርፍ ልቅ መተው ማለት አይደለም፡፡ የሀገር ኢኮኖሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅና ሸማቹ ማህበረሰብ እንዳይጎዳ ቁጥጥርና ወጥ የሆነ ስርዓት ማበጀት ከመንግስት በእጅጉ ይጠበቃል፡፡




ስለሸማቾች ጥበቃ እና ስለንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ስርጭት
የሸማች መብቶች (አንቀጽ 14)
ሸማች ማለት ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን ዋጋዉን ራሱ ወይም ሌላ ሰዉ የሚከፍልለት ሆኖ ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው ነው (አን. 2(4))፡፡ ማንኛውም ሸማች እንደ ሸማች የተለያዩ መብቶች በአዋጁ መሠረት የተቀመጠ ሲሆን እኚም መብቶች፡- መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት፣ አማርጦ የመግዛት፣ እንዲገዛ ያለመገደድ፣ በአክብሮት የመስተናገድ እና ካሣ እንዲከፍሉት የመጠየቅ ናቸው፡፡
ሀ. መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት፡- ማንኛውም ሸማች ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና አይነት አስመልክቶ በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት አለው፡፡
ለ. አማርጦ የመግዛት መብት፡- ሸማች መግዛት ወይም መሸመት የሚፈልገው የተለያዩ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ለመሸመት የሚፈልጋቸውን ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት መብት አለው፡፡
ሐ. እንዲገዛ ያለመገደድ፡- የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ መብት አለው፡፡
መ. በአክብሮት የመስተናገድ መብት፡- ሸማች ወይም ገዢ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በሚፈልግበት ጊዜ፣ በሚመርጥበት ጊዜ እና በሚገዛበት ጊዜ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድ መብት ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም ሸማች በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ መብት አለው፡፡
ሠ. ካሣ እንዲከፍሉት የመጠየቅ መብት፡- ሸማች ወይም ገዢ የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት የደረሰበት ጉዳት ካለ፣ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ ይህን ካሳ የመክፈል ግዴታ ያለባቸው በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ ሻጭነት፣ በችርቻሮ ሻጭነት ወይም በሌላ ማንኛውም ሁኔታ በአቅርቦቱ የተሳተፉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሸማቹ ከነዚህ አካላት በተናጠል ወይም በጋራ ካሳ የመጠየቅ መብት አለው፡፡

ይቀጥላል
ፌናን ተጊበሉ
የካቲት 15/2013 ዓ.ም

Comments

Be the first to add a comment