👉በአሜሪካ ምድር ዕድሜ ጠገቡ ድልድይ የት ይገኛል?

🚧ነገሩን በጥያቄ እንጀምረው—ለመሆኑ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ እስካሁን ድረስ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ አንጋፋ ድልድይ የት እንደሚገኝ ያውቃሉ?

«በአሜሪካ አንጋፋው ድልድይ» የሚለው ስያሜ እንደየአቆጣጠሩና እንደየአሠራሩ የተለያየ ትርጉም ሊኖረው ቢችልም፣ በታሪክ መዝገብ ቀዳሚነቱን ይዞ የሚገኘው «ፍራንክፎርድ አቨንዩ ድልድይ» (Frankford Avenue Bridge)ነው፤
ይህ ድልድይ በፊላደልፊያ ሰሜናዊ ምሥራቅ ግዛት በፔኒፓክ ወንዝ ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ዕድሜው ከ 320 ዓመታት በላይ ያስቆጠረና እስከ ዛሬ ድረስ መኪና የሚያስተናግድ ብቸኛ አንጋፋ የድንጋይ ቅስት ድልድይ ነው።

የዚህ ድልድይ ታሪክ የሚጀምረው እ.ኤ.አ በ1697 ከአሜሪካ ነፃነት መታወጅ ከረጅም ዓመታት በፊት ነው፣ የፔንሲልቬንያ መሥራችና እንግሊዛዊው ዊሊያም ፔን በወቅቱ በነበረው የቅኝ ግዛት ፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ፣ ከይዞታው ተነስቶ ወደ ታዳጊዋ የፊላደልፊያ ከተማ በቀላሉ መሻገር የሚያስችለው መንገድ እንዲሠራ ጠየቀ፤

በዚህም መሠረት የቅኝ ግዛቱ ምክር ቤት እ.ኤ.አ. መጋቢት 10 ቀን 1683 ባሳለፈው ውሳኔ፣ በ«ኪንግስ ሃይዌይ» መስመር ላይ በሚገኙ ወንዞች ሁሉ ላይ ድልድዮች እንዲገነቡ አዘዘ፤

ደንቡ ጥብቅ ነበር፤ እያንዳንዱ ድልድይ በ18 ወራት ውስጥ ተሠርቶ መጠናቀቅ ነበረበት፣ ወርዱም 10 ጫማ (ከ3 ሜትር በላይ) ሆኖ ለጋሪና ለፈረስ ትራፊክ አመቺ እንዲሆን በሁለቱም በኩል መከታ (ሀዲድ) እንዲኖረው ተወሰነ፣ የሚገርመው ደግሞ ግንባታው የተከናወነው በደመወዝ በሚሠሩ መሐንዲሶች ሳይሆን በአካባቢው ነዋሪዎች ጉልበት ነበር፤

በወቅቱ በሥራው ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ነዋሪ 20 ሽልንግ ይቀጣ ነበር። በዚሁ መልክ የሆልምስበርግ ነዋሪዎች ተረባርበው የገነቡት ይህ የፔኒፓክ መሻገሪያ፣ ፊላደልፊያን እንደ ትሬንተን፣ ኒው ዮርክ እና ቦስተን ካሉ ሰሜናዊ ከተሞች ጋር አገናኛት፤

ይህ ድልድይ ተራ መሻገሪያ ብቻ አልነበረም፤ የአሜሪካን ታሪክ በለወጡ ታላላቅ ሰዎች ኮቴ የተረገጠ ታሪካዊ ስፍራ እንጂ። በ18ኛው ክፍለ ዘመን በፈረስም ሆነ በጋሪ ከኒው ኢንግላንድ ግዛቶች ወደ ፊላደልፊያ የሚጓዙ መሪዎች ሁሉ በዚህ ድልድይ ላይ አልፈዋል፣ ለአብነት ያህል የአሜሪካው ሁለተኛው ፕሬዚዳንት ጆን አዳምስ እና ሌሎች የኮንቲኔንታል ኮንግረስ ልዑካን ይጠቀሳሉ፤

በ1756 በፊላደልፊያና በኒውዮርክ መካከል የመጀመሪያው የጋሪ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲጀመር ጉዞው 3 ቀናት ይፈጅ ነበር፣ በ1783 «ፍላይንግ ማሽን» የተባለው ፈጣን ጋሪ ሲፈጠር ግን ጉዞው ወደ አንድ ቀን ወረደ፤

የአሜሪካ አብዮት ሲፈነዳም የዚህ ድልድይ ስም አብሮ ይነሳል፣ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 24 ቀን 1775 ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ከደቡባዊ ቦስተን ተነስቶ ለአምስት ቀናት ያለማቋረጥ የጋለበ አንድ መልዕክተኛ፣ የሌክሲንግተን ውጊያ መጀመሩንና የአሜሪካ አብዮት መቀስቀሱን የሚያበስረውን አስቸኳይ ዜና ይዞ የገሰገሰው በዚህ ድልድይ ላይ ነበር፣ ከአራት ዓመታት በኋላ በ1789 ደግሞ ጆርጅ ዋሽንግተን የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ ለመሰየም ወደ ኒውዮርክ የተጓዘው በዚሁ ታሪካዊ መስመር ነበር፤

ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ድልድዩም አብሮ ዘመናዊ መልክ እየያዘ መጣ፦

በ1803፦ በድልድዩ ደቡባዊ ጫፍ ላይ የቀረጥ መክፈያ (Toll booth) የተተከለ ሲሆን መንገዱም ለመጀመሪያ ጊዜ ተነጠፈ። ይህ የቀረጥ ጣቢያ እስከ 1892 ድረስ ለአገልግሎት ውሏል፤

በ1893፦ ድልድዩ መጀመሪያ ላይ ለሁለት ጋሪዎች መተላለፊያ ጠባብ ስለነበር፣ የትራም (Trolley) ትራፊክን ለማስተናገድ ሲባል ሰፋ ተደርጎ ተሠራ፤

በ1950፦ ለመኪናዎች (Automobiles) ምቹ እንዲሆን በድጋሚ ተለጠጠ፤

በ2018፦v ድልድዩ ለ5 ወራት ያህል ተዘግቶ ትልቅ እድሳት ተደረገለት። የእግረኛ መንገዱ ታደሰ፣ የድንጋይ ግንባታው ጥገና ተደረገለትና በዚያው ዓመት መስከረም ወር ላይ እንደገና ተከፈተ፤

ይህ ድልድይ በ1970 ብሔራዊ የታሪክ ምሕንድስና መለያ ምልክት (National Historic Civil Engineering Landmark) የተባለ ሲሆን፣ በ1988 ደግሞ በብሔራዊ የታሪክ ሥፍራዎች መዝገብ ላይ ሰፍሯል፤

«የአሜሪካው አንጋፋ ድልድይ» የሚለው ስም እንደየባሕርያቸው ለሌሎችም ይከፋፈላል፤ የፍራንክፎርድ ድልድይ በአጠቃላይ መኪና ለሚያስተላልፍ መንገድ ቀዳሚ ቢሆንም፣ በየምድባቸው የሚከተሉትም ይጠቀሳሉ፦

1. ቾት ድልድይ (Choate Bridge)፦

በማሳቹሴትስ የሚገኝ ሲሆን የተገነባው በ1764 ነው። በአገሪቱ ውስጥ በሰነድ የተደገፈ አንጋፋው ባለ ሁለት ቅስት የድንጋይ ድልድይ ነው፤

2. ሃይድ ሆል የተሸፈነ ድልድይ (Hyde Hall Covered Bridge)፦

በኒው ዮርክ የሚገኝ ሲሆን የተገነባው በ1825 ነው። ከአገሪቱ አንጋፋ የእንጨት ጣራ የተሸፈነላቸው (Covered bridges) ድልድዮች ተርታ ይመደባል፤

3. ደንላፕስ ክሪክ ድልድይ (Dunlap's Creek Bridge)፦

በፔንሲልቬንያ የሚገኝ ሲሆን በ1839 የተገነባ ነው። በአሜሪካ የመጀመሪያው ከቀለጠ ብረት (Cast iron) የተሠራ ቅስት ድልድይ ነው፤

የብዙ ጥንታዊ ድልድዮች ዕድል በአሁኑ ወቅት ለእግረኛ መሄጃነት ወይም ለፓርክ መዝናኛነት መውለድ ነው፣ ለምሳሌ የሃይድ ሆል የእንጨት ድልድይ ዛሬ የሚገኘው በፓርክ ውስጥ እንጂ በዋናው አውራ ጎዳና ላይ አይደለም፤

ነገር ግን የፍራንክፎርድ አቨንዩ ድልድይ ታሪክ የተለየ ነው፣ ከተገነባ ከ320 ዓመታት በላይ ቢቆጠርም፣ ዛሬም ድረስ የ«US Route 13» ብሔራዊ መሥመር አካል ሆኖ መኪናዎችን እያስተናገደ ይገኛል፣ በአሁኑ ወቅት የ20 ቶን ክብደት ገደብ የተጣለበት ቢሆንም፣ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ እጅግ አንጋፋው ድልድይ ዛሬም ድረስ በመኪናዎ ሊሻገሩት የሚችሉ ሕያው የታሪክ ምስክር ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

@etconp

Comments

Be the first to add a comment