ጤና ይስጥልኝ!!
ይህ ሰሞን ክልሎቻችንም ሆነ ፌደራል መንግስታችን በስድስተኛው ዙር በተካሄደ ምርጫ ውጤት መሠረት ለቀጣይ አምስት ዓመት ሀገር ለመምራት በምስረታ እና ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ምስረታ የሚካሄደው በሕገመንግስቱ በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከሚቋቋሙት የመንግስት አካላት አንዱ የሕገ መንግስት ተርጓሚነት ሥልጣን የተሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 ስር ስለ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የተቀመጠውን እነሆ አንብቡልኝ!
1.የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤን ያደራጃል፡፡
2.የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠን መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ይወሰናል፡፡
3.በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የሕዝቦች እኩልነትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ያደርጋል፡፡ (ይንኑ ለማሳካት ከሚደረጉ ተግባራት በየዓመቱ በየክልሎቱ በተራ በበሚዘጋጅ ዓመታዊ የሕዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ያስታውሷል፡፡)
4.ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በጣምራ የተሰጡትን ሥልጣኖች ያከናውናል፡፡
5.በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ ይፈልጋል፡፡
6.የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፤ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጐማ የሚሰጥበትን ቀመር ይወስናል፡፡
7.በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ይለያል፡፡
8.ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል፡፡
9.የምክር ቤቱን የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ያቋቁማል፡፡
10.ምክር ቤቱ የራሱን አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤ ይመርጣል፤ የራሱን የሥራ አፈጻጸምና የውስጥ አስተዳደር ደንብ ያወጣል፡
ሲሳይ ሰማኝ (መስከረም 15/2014 ዓ.ም)

1 comment

Minilik
የ18/01/2014 የሰጣችሁን ስልጠና መልካም መሆኑን እየገለጸኩኝ በቴሌግራም ላይ ብትለቁልን እላለሁ