አባትነትን_እንዴት_ይረጋገጣል ?
አባትነት ለማረጋገጥ ሕጉ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡ [ የፌደራል የቤተሰብ ህግ ]
1,የሕግ ግምት [ከአንቀፅ 126 -130]
2, ልጅን መቀበል [ከአንቀፅ 131 -142]
3,የፍርድ ቤት ዉሳኔ ናቸዉ፡፡[ከአንቀፅ 143 -145]
ሀ. #የሕግ ግምት
የሕግ ግምት መሠረት የሚያደርገው ልጁ በሚፀነስበት ወይም በሚወለድበት ጊዜ በእናትና በአንድ ወንድ መካከል በሕግ የታወቀ ግንኙነት መኖርን በማረጋገጥ ነዉ፡፡ ይህም ልጁ ሲፀነስ ወይም ሲወለድ ከልጅ እናት ጋር በጋብቻ የነበረ ባል ወይም ጋብቻ ሳይፈጽም አብሯት የነበረው ወንድ የልጅ አባት ነዉ ብሎ ሕጉ ግምት ይወስዳል፡፡ በመሆኑም በልደት ምስክር ወረቀት አባቱ ሌላ ነው ተብሎ ቢፃፍም እንኳን ይህ የሕጉ ግምት አይቀየርም፡፡
ልጅ የተፀነሰው በጋብቻ ወይም አብሮ በኖሩበት ጊዜ ውስጥ ነው የሚባለው ጋብቻው ከተፈጸመበት ወይም አብሮ መኖር ከተጀመረበት ከ180 ቀናት በኋላ ልጅ ሲወለድ መሆኑ በሕጉ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ እንዲሁም ጋብቻው ፈርሶ ወይም አብሮ መኖር አብቅቶ ከሆነ ከፈረሰበት ወይም ካበቃበት ቀን ጀምሮ በ300 ቀናት ዉስጥ ልጅ የተወለደ እንደሆነ ነው፡፡ በመሆኑም የልጅ አባት የሚባለዉ በተመለከቱ ጊዜያት ከልጅ እናት ጋር አብሮ ያለው ወይም የነበረ ሰው ነው፡፡ ይህንን የሕጉን ግምት በሌላ ማስረጃ ማስተባበል አይቻልም፡፡
ለ. #ልጅነትን ስለመቀበል
በመቀበል አባትነት የሚረጋገጠዉ አባትየዉ ልጁን ልጄ ነዉ ብሎ በሚሰጠዉ ማረጋገጫ ስያረጋግጥ ነዉ፡፡ የአባትነት ማረጋገጫ በመስጠት አባትነት የሚረጋገጠዉ የልጅ አባት በሕግ ግምት ለመረጋገጥ የማይቻል ሲሆን ነዉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለዉ ልጁ የተፀነሰዉ ወይም የተወለደዉ እናት ከአንድ ወንድ ጋር በጋብቻ ወይም ያለጋብቻ በአብሮ መኖር ሥርዓት ሳትመሰርት ልጅ ሲወለድ ነዉ፡፡ በእንዲህ ባለ ሁኔታ አንድ ሰዉ አንድን የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ የእርሱ ልጅ መሆኑን አምኖ በመቀበል ቃሉን የሰጠ እንደሆነ የልጁ አባት ይባላል፡፡
መቀበሉን የሚገልጽበት ፎርም ወይም ሥርዓት በክብር መዝገብ ሹም ፊት በመቅረብ በሚሰጠዉ ቃል ወይም በጽሑፍ በሚያደርገዉ ኑዛዜ ወይም በሌላ በማናቸዉም ሥልጣን በተሰጠዉ ባለስልጣን በተረጋገጠ ሠነድ አማካኝነት ነዉ፡፡
በመርህ ደረጃ የመቀበል ቃሉን መስጠት ያለበት አባት ብቻ ነዉ፡፡ አባትየዉ ሞቶ ከሆነ ወይም ፈቃዱን ለመስጠት የማይችል በሆነ ጊዜ ከአባትየዉ ወላጆች አንዱ በእርሱ ስም ልጁን ሊቀበል ይችላል፡፡ አባት ነኝ ባዩ ቃሉን በሚገባዉ ሥርዓት ቢሰጥም እንኳን የልጁ እናት የተቀባዩ አባት እዉነተኝነት ያለዉ መሆኑን ካላመነች የተሰጠዉ ቃል በሕግ ፊት ዉጤት የለዉም፡፡ ይህ ማረጋገጫ ሳትሰጥ እናት ሞታ ወይም ፈቃድ መስጠት የማትችል ከሆነች ከእናት ወላጆች በአንዱ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በመርህ ደረጃ አባትነት መቀበል የሚቻለዉ የልጁ በሕይወት እያለ ብቻ ነዉ፡፡
ሐ. #በፍርድ ቤት ዉሳኔ
በሕግ የታወቀ ግኙኝነት ሳይኖር የሚወለድ ልጅ አባት ባይ ሰዉ በፈቃዱ ካልተቀበለ አባት የሚያጣበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነዉ፡፡ በመሆኑም በመካድ ወይም ባለመቀበል አባትነትን የሚያጡ ልጆች በፍርድ ቤት በሚሠጥ ዉሳኔ አባት እንዲያገኙ ህጉ ይኸንን ሶስተኛዉን ዘዴ አስቀምጧል፡፡
አባትነት በፍ/ቤት በሚሰጥ ዉሳኔ እንዲረጋገጥ: መሟላት ያለባቸዉ ሁኔታዎችም፤
ሀ. ልጁ በተፀነሰበት ጊዜ በእናቲቱ ላይ የመደፈር ወይም የመጠለፍ ተግባር የተፈጸመባት ሲሆን፣
ለ. ሆነ ተብሎ በተደረገ የተንኮል ድርጊት ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም አገባሻለሁ በማለት ተስፋ ቃል በመስጠት ወይም በሌላ ተመሳሳይ መንገድ ልጁ በሚፀነስበት ጊዜ ከእናት ጋር ፆታዊ ግኝኙነት የተፈጸመባት ሲሆን:
ሐ. አባት ነዉ በተባለዉ ሰዉ የተጻፈና በማያሻማ ሁኔታ አባትነቱን የሚያረጋግጡ ደብዳቤዎች ወይም ሌሎች ጽሑፎች ሲኖሩ፣
መ. በሕግ የታወቁ ግንኙነት ሳይኖራቸዉ የልጁ እናትና አባት የተባለዉ ሰዉ በሕግ በተመለከተዉ የእርግዝና ጊዜ ቀጣይነት ባለዉ ሁኔታ በግብረ ሥጋ ግንኙነት አብረዉ የኖሩ እንደሆነ ነዉ፡፡
ከእነኝህ ሁኔታዎች በአንዱ ምክንያት ልጅ ተፀንሶ ከሆነ በድርጊቱ ላይ የነበረዉ ወንድ አባት ተብሎ በፍርድ ቤት ይወሰናል፡፡
mr zee

Comments

Be the first to add a comment