👉በ28 ዓመታት ውስጥ በ805 ቢሊዮን ብር ወጪ ከ153 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ አዳዲስ መንገዶች ተገንብቷል

🚧ኢትዮጵያ ከዝቅተኛ የመንገድ መሠረተ-ልማት ተነስታ አሁን ላይ ሰፊ፣ ዘመናዊና የኢኮኖሚ ኮሪደሮችን የሚያገናኝ የመንገድ መረብ ባለቤት ለመሆን በቅታለች፤

ይህ በየምዕራፉ የተተገበረው የመንገድ ዘርፍ የልማት ፕሮግራም የሀገሪቱን የጉዞ አቅጣጫ በተቀናጀ መልኩ የመራ ሲሆን፣ የመንገድ ግንባታ ከቁጥር ባለፈ ዘላቂነትና ተደራሽነትን ያረጋገጠ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፤


በ1989 ዓ.ም የተጀመረው ይኸው የመንገድ ዘርፍ የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ የመንገድ ልማት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የመንገድ አውታሩን ማስፋት፣ ጥራትን ማሻሻል፣ የጥገና ሥርዓትን ማጠናከርና ተቋማዊ አቅምን መገንባት ላይ ያተኮረ ነበር፤

በዚሁ መሠረት ከ1989 እስከ 1994 ዓ.ም በተተገበረው መጀመሪያው የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም፣ ዋና ትኩረቱ አዲስ አበባን ከክልል ዋና ከተሞች፣ ከንግድ ማዕከላትና ከወደብ መስመሮች ጋር የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎችን ማሻሻል ላይ በመሆኑ 8 ሺህ 709 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶና ታድሶ ለአገልግሎት በቅቷል፤

ይህንን ተከትሎ ከ1995 እስከ 1999 ዓ.ም በተከናወነው ሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮግራም የመንገድ አውታርን ማስፋት፣ የገጠር ተደራሽነትን ማሻሻልና አዳዲስ መንገዶችን መገንባት ተቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶት 11 ሺህ 589 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቷል።


ጉዞው በዚሁ ሳይገታ ከ2000 እስከ 2002 ዓ.ም በነበረው ሦስተኛው ምዕራፍ፣ ነባር የጠጠር መንገዶችን ወደ አስፋልት ማሳደግ እንዲሁም አዳዲስ አገናኝና ዋና መዳረሻ መንገዶችን መዘርጋት ላይ በማተኮር አሥራ 2 ሺህ 395  ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት ውሏል።

የገጠር አካባቢዎችን ከመንገድ አውታር ጋር ማገናኘትና ተደራሽነትን ማስፋት ልዩ ትኩረት ያገኘው ደግሞ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም በተተገበረው አራተኛው ፕሮግራም ሲሆን፣ በዚህ ወቅት 85 ሺህ 86, ስምንት መቶ ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የተለያዩ መንገዶች ተገንብተዋል።

ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም የነበረው አምስተኛው የመንገድ ዘርፍ የልማት ፕሮግራም ደግሞ የመንገድ ልማትን ከጥራት፣ ከዘላቂነትና ከቴክኖሎጂ ጋር ያስተሳሰረ ምዕራፍ የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ ፕሮግራም የመጀመሪያ ሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ በአጠቃላይ 27 ሺህ 210 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ መንገዶች ግንባታ ተከናውኗል።

በመጨረሻም ከ2012 እስከ 2017 ዓ.ም በተተገበረው ስድስተኛው የመንገድ ዘርፍ የልማት ፕሮግራም 28 ሺህ 949 ኪሎ ሜትር የፌዴራል፣ የክልልና የወረዳ መንገዶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

ይህ መጠነ ሰፊ ክንውን የሀገሪቱን አጠቃላይ የመንገድ አውታር በ1989 ዓ.ም ከነበረበት 26 ሺህ 550  ኪሎ ሜትር ብቻ ተነሥቶ አሁን ላይ ወደ 182 ሺህ 232 ኪሎ ሜትር እንዲያድግ አድርጎታል።

ባለፉት 28 ዓመታት በተተገበሩት በእነዚህ ስድስት ተከታታይ ፕሮግራሞች በአጠቃላይ 805.6 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ግዙፍ መዋለ-ንዋይ ፈሰስ ተደርጓል።

በአጠቃላይ እነዚህ ፕሮግራሞች የመንገድ አውታርን በማስፋት ብቻ ሳይወሰኑ፣ የጥራት ደረጃን ከፍ ማድረግ፣ የገጠርና የከተማ ትስስርን ማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ኮሪደሮችን ማሳደግና የሀገር አቀፍ ልማትን ማፋጠን የቻሉ የለውጥ ምዕራፎች በመሆን ወደ ተሻለ የዕድገት ጎዳና የምትጓዝ ኢትዮጵያን መገንባት ችለዋል።

Via ERA

@etconp

Comments

Be the first to add a comment