👉የአማካሪ ሲቪል ኢንጂነር
ኃላፊነት እና ድርሻ

💫የአማካሪ ሲቪል ኢንጂነሮች ኃላፊነት እና ድርሻ በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ውስጥ የሚሰጠው ትኩረትም ሆነ አስገንቢ ድርጅቶችም ሙያውን በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው።

🚧ብዙውን ጊዜ አስገንቢ ድርጅቶች ከአማካሪዎች ጋር ውል የሚፈራረሙት ግንባታውን ለማስጀመር የተጣለባቸውን መስፈርት ለማሟላት ብቻ ሲሉ ነው።

▶️ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ በውሉ ላይ አማካሪ ነኝ ብሎ ፊርማውን የሚያኖረው በተለይ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘ ሲቪል ኢንጂነር፣ ፍቃደኛ ሆኖ በመፈረሙ ከሚከፈለው በተለይ ሙያውን ከሚያራክስ አነስተኛ ክፍያ ውጪ፣ የተማረውን ሙያ የሚተገበርበት ዕድልም በጣም አነስተኛ ነው፡፡

⏺በተለይ አስገንቢው የግል ባለሀብት ከሆነ በተጠየቀው መንገድ ቢሮ ተቀምጦ እየፈረመ እና የተሰጠውንም ፎቶ ኮፒ እያያዘ ለባለሀብቱ ከመስጠት ውጪ፣ ግንባታው የት እንደሚካሄድ እንኳ የማወቅ እድሉ ወይም ፍላጎቱ የጠበበ ወይም እንደሌለ የሚቆጠር ነው።

⏹በደቡብ አፍሪካ የኮንስልቲንግ ሲቪል ኢንጂነር ኢንስቲቲዩት፣ በአፍሪካ የአማካሪ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኃላፊነት ድርሻ ትኩረት ተነፍጎታል በማለት በቅርቡ ለንባብ ያበቃው ጽሑፍ ዓላማውም የአማካሪ ሲቪል ኢንጂነር ኃላፊነት እና ድርሻ በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ውስጥ የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

#⃣እንድ ጽሑፍ ማብራሪያ፣ የአማካሪነት ሙያ አዳዲስ ችግሮችን እየተጋፈጠ ምላሽ መስጠት ለማይችል ሰው የሚመች ወይም የሚገባ የሥራ መስክ እንዳልሆነ በቅድሚያ መገንዘብ ይገባል።

*⃣በሂደት የሚገጥሙትን ችግሮች እየተጋፈጠ እና መፍትሄ እየሰጠ ሙያውን እያዳበረ መሄድ ለሚፈልግ የሲቪል መሀንዲስ ደግሞ እንደ ትልቅ ስጦታ የሚቆጠር ነው፡፡ ምክንያቱም ሙያው ከሲቪል ኢንጂነሪንግ ሙያ በተጨማሪ የቢዝነስ እና የማኔጅመንት ሙያ ወይም ክህሎትን ስለሚጠይቅ፣ ይህንን ጥምር ሙያ በተግባር ላይ ለማዋል እና ኢንጂነሩ በቀጣይነት ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ኢንተርፕሩነር ወይም የአማካሪ ድርጅት ባለቤት የመሆን ዕድልን ስለሚፈጥርለት ነው፡፡

⏸ከዚሁ በተጨማሪ፣ እንደ ዶክተር እና የህግ ባለሙያ ከመደበኛ ሥራ ውጭ በትርፍ ጊዜ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚያስችል አጋጣሚዎችንም የሚፈጥር መሆኑን ለመመልከት ወደ ዝርዝር መረጃዎች እንሻገር።

▪️አማካሪ ሲቪል ኢንጂነር ምንድ ነው?
  
⏺አማካሪ ኢንጂነር፣ በሲቪል ኢንጂነር ወይም በአማካሪ ኢንጂነር  የፕሮፌሽናል ሙያ የተመረቀ፣ እንደሚኖርበት ሀገር ህጋዊ ፍቃድ አውጥቶ ከመሰሎቹ ጋር በመቀናጀት ወይም የግል ድርጅት ከፍቶ ከአስገንቢ ባለሀብቶች፣ ድርጅቶች ግለሰቦች ወይም ከመንግስት ተቋማት ጋር ውል በመፈረም የአማካሪነት አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ ነው፡፡

⏺የአማካሪነት ሙያ ፍቃድ ያገኘ ሰው፣ የአማካሪነት አገልግሎት ሲሰጥ ከጥሬ ዕቃ አምራቾች፣ ከዕቃ አቅራቢዎች እና ከኮንትራክተሮች ጋር ውስጣዊ የጥቅም ግንኙነት መፍጠር እንደማይገባው እና በህግም ተጠያቂ የሚያደርገው አሠራር በውሉ ላይ መስፈር እንዳለበት የሙያው መሠረታዊ ህግ መሆኑ በጥልቅ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

⏺ከዚህ የህግ አግባብ ወጪ፣ አንድ አማካሪ ከተመረቀበት የኢንጂነሪንግ ሙያ በተጨማሪ ተያያዥነት ባላቸው ዘርፎች የመሠማራ መብት ሊጠበቅበት ይገባል። በሌላ አነጋገር፣ አማካሪ ኢንጂነር ስፔሻላይዝ ባደረገበት የኮንስትራክሽን ዘርፍ የአማካሪነት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ ተጨማሪ ዕውቀት በሚጠይቁ ዘርፎች ሌሎችን እየማከረ ወይም በስሩ እያቀፈ በርካታ የተለያዩ ድርጅቶች እና ደንበኞችን በመያዝ የማማከር አገልግሎት መስጠት የሚችል ባለሙያ ነው።

▪️የአማካሪ ኢንጂነር የሥራ ድርሻዎች

♻️ማማከር

📈ግንባታዎች በተቀመጠላቸው መስፈርት፣ ጥራት እና ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ለማድረግ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሚያዙት እና ደንበኞች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት እንዳስፈላጊነቱም በቦታው በመገኘት የማማከር ወይም የኤክስፐርት ሙያ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡

🔰ማጥናት/መመርመር

📯አብዛኛው በማማከር ሼል ውስጥ ግንባታዎችን በማጥናት እና በመመርመር የሚሰጠው   አገልግሎት ስሌት እና ትንተናን የተመረኮዘ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ የምክር አገልግሎቶች የግንባታ መሣሪያዎች እና የግንባታ ሂደቶችን በቦታው ተገኝቶ ማጥናት እና መመርመርን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የሁለቱም የምርመራ ወይም የጥናት ሂደቶች ዋና አላማ፣ ሥራውን በሚያከናውኑ የተለያዩ ባለሙያዎች የቀረቡ ሪፖርቶችን ትክክለኝነት ለማጣራት ነው።

✂️ኢንጂነሪንግ ዲዛይን

🗂ኢንጂነሪንግ ዲዛይን የሚገነባውን ህንፃ አጠቃላይ ቅርፅ፣ ስፋት፣ ርዝመት እና በየእርከኑ የሚገነቡ የህንፃውን ክፍሎች በመወሰን፣ በንድፍ እና በካርታ የማስቀመጥ ሥራ ነው፡፡ እነዚህ ካርታ እና ንድፎች ብሉፕሪንት ተብሎ በሚታወቀው ወረቀት በድሮዊንግ ከማስፈር በተጨማሪ፣ በጽሑፍ የሚቀርቡ ዝርዝር መረጃዎችን የሚያካትቱ ናቸው፡፡

📝የፕላኑ ዝርዝር መረጃዎቹ የሚዘጋጁት ግንባታውን ለሚያካሄደው ኮንትራክተር እና ለባለሙያዎች ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ዕቃዎች አይነት፣ ብዛት እና መጠንን የሚያመልክቱ "ቢል ኦፍ ኳንቲቲስ" ከዲዛይኑ ጋር ሊቀርቡ ይችላሉ።

🔗የግንባታ፣ የኮንራት ውል እና ጨረታን ማዘጋጀት ብሎም ማማከር
   
📏አማካሪ ኢንጂነሮች ከደንበኞቻቸው በሚቀርብላቸው ጥያቄ መሠረት ሥራ ተቋራጭ፣ ዕቃ ግዢ እና አቅራቢ ኩባንያ ምርጫ ላይ የመምረጥ እና የማማከር አገልግሎት በመስጠት ፕሮፎርማ ይሠራሉ፡፡ በመንግሥታዊ የግንባታ ተቋሞች አማካሪዎች፣ የኮንትራት ዶክመንቶችን ዲዛይኖችን ጨረታዎችን የማዘጋጀት እና የመምረጥ አገልግሎት ይሰጣሉ። ጨረታዎቹ ህግን እና ግልፅነትን በተሞላ መንገድ መካሄድን የመከታተል እና በቦታው ተገኝተው የመለየት የመምረጥ ሥራ ይሰራሉ።

📌ግንባታዎችን መቆጣጠር 

📐አማካሪዎች የሚሰጡት ግንባታዎችን የመቆጣጠር ሥራ በመስክ እየተገኙ እና በቢሮ ተቀምጠው የሚሰጡ አገልግሎቶችን ያካተቱ ናቸው። በመስክ በቢሮ የሚሰጡ የግንባታ ቁጥጥር አገልግሎቶች የሚባሉት፦

▪️በፕሮግራም የሚመራ የሳይት ጉብኝት፣
▪️ደንበኛ ወይም ባለቤትን የማማከር፣
▪️በፕላን ዝግጅት፣ በዝርዝር ጉዳዮች አዋጪ እና ተመራጭ የሆኑ አማራጮችን ማዘጋጀት፣
▪️ የግንባታ ድሮዊንግ እና ዳታዎችን ትክክለኝነት መፈተሽ፣
▪️ የኮንትራክተሮችን ክፍያ መገመት እና እንዲከፈላቸው መፍቀድ፣
▪️ከኮንትራክተሮች ጋር የሚካሄድ የኮንትራት ውልን ማዘጋጀት፣
▪️ግንባታዎች በተቀመጠላቸው ንድፍ እና ዝርዝር ጉዳዩች መሠረት መጠናቀቀቸውን ማረጋገጥ፣
▪️በግንባታ ውስጥ የሚዘረጉ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ውኃ የመሳሰሉ መሥመሮች መነሻ፣ የሚሄዱበትን መሥመር እና መጨረሻቸውን የሚያሳይ ንድፍ ማዘጋጀትን የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡

🗞ህጋዊ ድጋፍ መለገሰ

🔎አማካሪዎች በኮንትራክተሮች እና በባለሙያዎች መካከል የሚደረግ ህጋዊ ውልን ከማዘጋጀት እና ከማስፈፀም በተጨማሪ፣ እንደየአስፈላጊነቱ ችግሮች ሲፈጠሩ በፍርድ ቤት ቀርበው የምስክርነት አገልግሎት የመስጠት መብት እና ግዴታ እንዳለባቸው በመረጃው ላይ ሠፍሯል።

@etconp

1 comment

አዉን በጣም ትክክለኛ እውነተኛ መረጃ ነው