የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ዋስትና የሚቆይበት ጊዜ እና ተግባራዊ አፈጻጸሙ!
***
ዋስ በወንጀል የተጠረጠረ ወይም የተከሰሰ ሰዉ የተጠረጠረበት የወንጀል ጉዳይ ምርመራ እስኪጠናቀቅ ወይም ክሱ በፍርድ ቤት ታይቶ ዉሳኔ እስኪያገኝ ድረስ በሚፈለግበት ጊዜ እና ቦታ ለማቅረብ ግዴታ ገብቶ ተጠርጣሪዉ ወይም ተከሳሹ ከእስር እንዲለቀቅ የሚያደርግ መተማመኛ መሆኑን ይገልጸዋል፡፡ በወንጀል ጉዳይ ከዋስትና ጋር በተያያዘ ከሚነሱ ጥያቄዎች ዉስጥ አንድ ዋስትና ለምንያህል ጊዜ፣ እስከመቼ ድረስ ተይዞ ይቆያል የሚለዉ ምላሽ የሚያስፈልገዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ ይህ የዋስትና ቆይታ ጊዜ በወንጀል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በፍትሐ ብሔር ጉዳይም መሰረታዊ የሚባል ነዉ፡፡ በልምድ እንዳየነዉ ከሆነ አንድ ሰዉ ታስሮ በዋስ መፈታቱን፣ ዋስትና አስይዞ መዉጣቱን እንጅ ያስያዘዉ ዋስትና እስከመቼ ድረስ ተይዞ እንደሚቆይ ጉዳዩ አይደለም፡፡
እስኪ ታስረዉ በዋስ ከተፈቱ ሰዎች ዉስጥ ስንቶቹ ጉዳያቸዉን ተከታትለዉ ዋስትናቸዉን አስመልሰዋል? ዋስትና ገቢ የሚደረግባቸዉ የፍርድ ቤቶች ሞዴል 85 ስንት ያልተመለሰ የዋስትና ገንዘብ እንደያዙ ቀርተዉ ይሆን? ጥናት የሚያስፈልገዉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዋስትና በሞዴል 85 የተያዙ ገንዘቦች የብዙ ዓመታት ጥርቅም ያልተወራረደ ሂሳብ ያላቸዉ ናቸዉ ፡፡
ለዚህ ሁሉ ምክንያት ዋስትና የሚያስይዙ ሰዎች እንኳን በዋስ ወጣሁ እንጅ ገንዘቡን መንግስት ይብለዉ የሚል የራስን መብት የመተዉ ችግር ቢሆንም ቁልፍ ችግሩ ያለዉ ሕግ አተገባበሩ ላይ ነዉ፡፡ ዋስትና የሚሰጥበት እና የሚፈጸምበት ሥርዓት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት ሕጉ እና በሌሎች ልዩ ሕጎች ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በወንጀል ጉዳይ የሚሰጥ ዋስትና የእድሜ ልክ ሳይሆን በጊዜ ተገድቦ የሚሰጥ ነዉ፡፡ በጊዜ የመገደቡም ዋና ዓላማ ከተጠርጣሪዎች እና ከተከሳሾች አፋጣኝ ፍትሕ ከማግኘት መብት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነዉ፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት ሕጉ አንቀጽ 71 ዋስትና የሚቆየዉ ፍርድ ቤቱ ለወሰነዉ ጊዜ ብቻ እንደሆነ በአስገዳጅ አስቀምጦታል፡፡ ዋስትናዉ እንዲቆይ በተወሰነበት ጊዜ ጉዳዩ ባያልቅ እንኳን ዋስትናዉ የሚቆይበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ ሊያራዝመዉ እንደሚችል በድንጋጌዉ ተመላክቷል፡፡
ሕጉ በተግባር ሲታይ ግን አንድ በወንጀል ጉዳይ የሚሰጥ ዋስትና ጊዜ ተቀምጦለት ሲወሰን አይታይም፡፡ ፍርድ ቤቶች አንድን ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ በዋስ እንዲወጣ ሲወስኑ ዋስትናዉ የሚቆይበትን ጊዜ ሲያስቀምጡ አይታይም፡፡ ይህም ፖሊስ እና ዓቃቤ ሕግ አንድን የወንጀል ጉዳይ አፋጥነዉ ወደ ዕልባት እንዳያደርሱ የማድረግ ዉጤት ከማስከተሉ አልፎ የወንጀል ተጠርጣሪ እና ተከሳሾችም ዋስትና ማስያዛቸዉን እንጅ ዋስትናን ለማስመለስ ጥረት እንዳያደርጉ ምክንያት ሲሆናቸዉ ይታያል፡፡
Comments
Be the first to add a comment