የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ተመን ማሻሻያ ሊያደርጉ ነው!
ዋዜማ ራዲዮ- እንደዘገበችው
በፌደራል ፍርድ ቤቶች ለሚደረግ የዳኝነት አገልግሎት ከእስካሁኑ ከፍ ያለ የዳኝነት ክፍያ የሚያስከፍል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ውሳኔን እየጠበቀ ነው። ከፌደራል ፍርድ ቤቶች በተውጣጡ ባለሙያዎች እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት አማካኝነት የተዘጋጀው ይህ አዲስ ረቂቅ ደንብ ከ60 አመታት በላይ ሲያገለግል የነበረውን የክፍያ ተመን የሚቀይር ሲሆን ፍርድ ቤቶች የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት የሚያጸድቅላቸውን በጀት ብቻ ሳይጠብቁ በገንዘብ ራሳቸውን እንዲደግፉ የሚያግዛቸው እንደሚሆን ይታመናል።
በ1945 ዓ.ም ወጥቶ እስካሁን በስራ ላይ ባለው ተመን መሰረት ተገልጋዮች አሁን የሚከፍሉት ትንሹ የክፍያ መጠን የክስ መጠኑ እስከ 10 ብር ድረስ ለሆነ ክስ 50 ሳንቲም ሲሆን ይህም እንደየ ክሱ ገንዘብ መጠን ክፍያው በትንሹ እያደገ ይሄድና የመጨረሻው የክፍያ መጠን የክስ መጠኑ ከዘጠኝ መቶ ሺህ እስከ አንድ ሚልየን ብር ለሚደርስ ክስ 12,850 ይሆናል። ከአንድ ሚልየን ብር በላይ ላለ የክስ መጠን የዳኝነት የሚከፈልበት ግልጽ ደንብ ባለመኖሩ ምክንያት ፍርድ ቤቶች ወጥነት የሌለው አሰራር ሲከተሉ ቆይተዋል። በአሁን ጊዜ ፍርድ ቤቶች እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ያላቸው እና በቢልየን ብር የሚተመኑ የፍርድ ጉዳዮችን የሚያዩ ሲሆን ከነዚህም የሚፈለገውን ያህል የዳኝነት ክፍያ ሳያስከፍሉ ቆይተዋል።
ረቂቅ የዳኝነት ክፍያ ደንቡ ክፍያዎችን በመቶኛ የአከፋፈል መጠን ያዘጋጀ ሲሆን የመጀመሪያ ክፍያውም እስከ 20,000 ብር ድረስ የገንዘብ መጠን ላላቸው ጉዳዮች 8 በመቶ ያስከፍላል። ረቂቁ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ላላቸው የክስ ሂደቶችም የገንዘብ አከፋፈል ስርዓት ያለው ሲሆን የክስ ገንዘቡ እያደገ በመጣ ቁጥር የመቶኛ መጠኑም ከ8 በመቶ እያነሰ የሚመጣ ይሆናል። ዝቅተኛው የመቶኛ አከፋፈልም አንድ በመቶ ሲሆን ይህም የገንዘብ መጠናቸው ከ 200 ሚልዮን በላይ ላሉ ክሶች ይሆናል።
በገንዘብ ሊተመኑ ለማይችሉ አቤቱታዎችም ረቂቅ ደንቡ የክፍያ ደንብ ያወጣ ሲሆን በዚህም መሰረት በፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ተገልጋዮች አንድ ሺህ ብር መክፈል ይኖርባቸዋል። በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ደግሞ ተገልጋዮች አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር መክፈል ይኖርባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ረቂቅ ደንቡ ለዳኝነት አገልግሎት የማይከፈልባቸውን ጉዳዮች ያስቀመጠ ሲሆን እነዚህም በህግ በደሃ-ደንብ እንዲከራከር ለተፈረደለት ሰው እና የሰብዓዊ መብት ይከበርልኝ ለሚሉ አቤቱታዎች ነው። ሆኖም የሰብዓዊ መብት ይከበርልኝ አቤቱታዎች ከንብረት ክርክር ጋር የተያያዙ ከሆኑ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ።
Comments
Be the first to add a comment