የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ሰላም!
የደንብ መተላለፍ ድርጊቶችን የሚከላከል፣ እርምጃ የሚወስድና የሚያስወስድ ባለሙያ (ፓራሚሊተሪ ኦፊሰር) ነዎት?
እንግዲያውስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣንን አደረጃጀት፣ አሰራር እና የፓራሚሊተሪ ሠራተኞች አስተዳደርን ለመወሰን በወጣው ደንብ ቁጥር 150/2015 አንቀጽ 45 መሰረት መቼና ለምን ኃይል መጠቀም እንደሚችሉ የተደነገገውን ልናጋራዎት ወድደናልና ያንብቡን!
1/ ኃይል መጠቀም የሚቻለው መቼ ነው?
ኦፊሰሩ ኃላፊነቱን በሚወጣበት ወቅት፥-
ሀ) ኃላፊነቱን እንዳይወጣ የሚያደርግ ግልጽ ተቃውሞ ካጋጠመው፤
ለ) ሌሎች አማራጮችን ሲያጣ፤ እና
ሐ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣንን በማሳወቅ
ብቻ ተመጣጣኝ ኃይል ሊጠቀም ይችላል።
2/ ሀይል መጠቀም የሚቻለው ምን ሲያጋጥም ነው?
ሀ) በራሱ ወይም በስራ ባልደረባ ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመከላከል፤
ለ) የተወረሰ ንብረትን ከደንብ መተላለፍ እርምጃ አወሳሰድ ኦፊሰሩ ወይም ህገ-ወጡን ከሚቀለብሰው ግብረ-ሀይል በመንጠቅ ለማምለጥ የሚሞክረዉን፣ ንብረቱን ነጥቆ በመያዝ በማምለጥ ላይ ያለን ህገወጥ ድርጊት ፈጻሚ ለማስቆም ነው።
3/ ሀይልን ከሕግ ውጪ መጠቀም ምን ያስከትላል?
የተሰጠውን ሥልጣን ካላአግባብ በመጠቀም በግለሰብ አካል እና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ኦፊሰር ከባድ የዲስፕሊን ጥፋት እንደፈጸመ ተቆጥሮ፥-
ሀ) እስከ አራት ወር የሚደርስ ደመወዙን ሊቀጣ፣
ለ) እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ለሚደርስ ጊዜ ከሥራ ደረጃው እና ደመወዙ ዝቅ ሊደረግ፣
ሐ) ከሥራው ሊሰናበት ይችላል።
መውጫ፥- ኦፊሰሩ የሚጠቀመው ተመጣጣኝ ሀይል ኃላፊነቱን እንዳይወጣ የሚያደርገውን መሰናክል ለማስቀረት ብቻ መሆን አለበት!
የዲሲፕሊን እርምጃ የፓራ-ሚሊተሪ ሠራተኛውን የወንጀልና የፍትሐብሔር ተጠያቂነት አያስቀርም!
መስከረም 18 ቀን 2016 ኣ.ም
ፋሲካ አጌና (የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት አቃቤ-ሕግ)
Comments
Be the first to add a comment