👉 የሴራሚክ ምርትን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ ሊቆም ነው

ኢትዮጵያ እስከ ስድስት ወራት በሚደረስ ጊዜ ውስጥ የሴራሚክ ምርትን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ እንደምታቆም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህን ያሉት "ከተሞች በአዲስ ምናብ" በሚል ርዕስ ከቃና ቴሌቪዥን ጋር በተደረገ ቆይታ ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው፤ የሀገሪቱን ፍላጎት ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚተርፉ ግዙፍ የሴራሚክ ፋብሪካዎች ግንባታቸው እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ፋብሪካዎች ተጠናቅቀው ማምረት ሲጀምሩ፣ ሴራሚክን ከውጭ የማስገባት ፍላጎት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀረፍ አስረድተዋል።

በተጨማሪ ከአንድ ዓመት ወይም ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የሀገሪቱን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ በሁሉም ዓይነት የመስታወት ምርቶች ራስን ለመቻል እየተሠራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

መስታወትን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት መታቀዱንም አብራርተዋል።

በግራናይት እና በማርብል ዘርፍም በርካታ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ የጠቀሱት ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ጥራት ላይ ትኩረት ከተደረገ ከብረት ጥሬ ማዕድን በስተቀር መብራት፣ መኪና እና የመሳሰሉትን ለመሥራት በሀገር ውስጥ ከፍተኛ አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።

ለብረት ማዕድን ፍለጋም ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመው፤ ይህም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚባክነውን የውጭ ምንዛሬ በእጅጉ እንደሚቀንስ አመልክተዋል።

Via ፕሬስ ጋዜጣ

Comments

Be the first to add a comment