#ፍቺ_እና_ንብረት_ክፍፍል |የሰበር ችሎት አስገዳጅ መርሆች

=====================================
​በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ውስጥ ንብረት ሲከፋፈል የሚተገበሩ ዋና መርሆዎች እነሆ። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጣቸው እነዚህ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜዎች ንብረትዎ የግል ወይስ የጋራ መሆኑን ይወስናሉ!

​I. የጋራ እና የግል ሀብት መለያ

1. ቅድመ ጋብቻ ንብረት:- የግል ነው!
በውርስ ወይም በስጦታ በግል ያገኛችሁት ንብረት ሁልጊዜ የግል ነው። (የፌዴራል ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 57)

2. የካሳ ንብረት:- ​በልማት ምክንያት በመንግስት የተሰጠ የካሳ ቤት ወይም ገንዘብ፣ ለተሰጠው ተጋቢ የግል ንብረት ሆኖ ይቆያል — የጋራ ውል ከሌለ። (ሰ/መ/ቁ 252723)

​II. ከግል ወደ ጋራነት የሚደረግ ለውጥ

1. ዓቢይ መሻሻል (Major Improvement):- በውርስ የተገኘ ቤት ቢሆንም እንኳ፣ በቤቱ ላይ ከነባር ቤቱ ዋጋ እጥፍ በላይ የሆነ ወጪ ወጥቶ ማሻሻያ ከተደረገ ቤቱ የጋራ ንብረት ነው ተብሎ ሊወሰን ይችላል። (ሰ/መ/ቁ 241998

2. አክሲዮን ዕድገት (Stock Growth):- ​ከጋብቻ በፊት የተገዛ የአክሲዮን ድርሻ በትዳር ውስጥ ያሳየው የዋጋ ዕድገት ወይም ትርፍ የጋራ ሀብት ነው። (ሰ/መ/ቁ 251014)

​III. የሕግ ግምት እና የማስረዳት ሸክም

​1. በአንዱ ስም መመዝገብ (Registration): በትዳር ውስጥ በግብይት የተገኘ ንብረት በአንዱ ስም ቢመዘገብም፣ የግል ንብረትነቱን የማረጋገጥ ሸክም ያለበት ንብረቱ የግል ነው የሚለው ተጋቢ ነው። (ሰ/መ/ቁ 239542)

2. የትዳር ገንዘብ አጠቃቀም :- ገንዘብ የትዳር ጊዜ ውጤት መሆኑ ከተረጋገጠ፣ "ለጋራ ጥቅም አልዋለም" የሚል ወገን ነው ማስረጃ አቅርቦ ሊያረጋግጥ የሚገባው። (ሰ/መ/ቁ 239911 እና 242630)

3. ተለያይቶ መኖር (Separation):- ጋብቻው በሕጋዊ ሥርዓት እስካልፈረሰ ድረስ፣ ተጋቢዎች ተለያይተው ቢኖሩም በዚያ ጊዜ የተፈራ ንብረት የጋራ ንብረት ነው በሚለው ግምት ውስጥ ይጠቃለላል። (ሰ/መ/ቁ 252442)

​IV. የክፍፍል መርሆዎች እና እኩልነት 50/50

​1/ክፍፍል በዓይነት (In Kind) ቀዳሚ ነው!
​ፍርድ ቤቶች ንብረቱ በዓይነት ሊከፋፈል የሚችልበትን ሁኔታ ሳያጣሩ በቀጥታ እንዲሸጥ መወሰን የሕጉን መርህ ይጥሳል። (ሰ/መ/ቁ 242840)

2. የግንባታ ክፍፍል (Improvements) :- በጋራ የተሰሩ ግንባታዎች ክፍፍል ሲደረግ፣ የስር ፍርድ ቤቶች የግንባታውን ግምት ብቻ እንዲወስዱ መወሰን የሕገ መንግሥቱን የእኩልነት መርህ የጣሰ ነው። ንብረቱ ይዞታውን ጨምሮ በእኩል ይካፈላል። (ሰ/መ/ቁ 247067)

​3. ፕሮቪደንት ፈንድ እና አክሲዮን (Provident Fund & Stocks):- ​በትዳር ጊዜ ከተጋቢዎች ገቢ ላይ የሚጠራቀመው ፕሮቪደንት ፈንድ ወይም የአክሲዮን ድርሻ የጋራ ሀብት ተደርጎ በዓይነት እኩል መከፋፈል አለበት። (ሰ/መ/ቁ 243551 እና 190650)

​4. የጋራ ንብረት ላይ መኖር:- አንድ የጋራ ባለሀብት በጋራ ንብረት ላይ በመኖሩ ብቻ ለሌላኛው የቤት ኪራይ እንዲከፍል አይገደድም። (ሰ/መ/ቁ 212598)

​V. የጋብቻ ውል፣ ኑዛዜና ይርጋ

1. የጋብቻ ውል መጽደቂያ (Validation):- ​ከጋብቻ በኋላ የሚደረግ የንብረት ክፍፍል ስምምነት ወይም ውል ማሻሻያ ሕጋዊ ውጤት እንዲኖረው በሰነዶች ማረጋገጫ ጽ/ቤት (Sene) መመዝገቡ ብቻውን አይበቃም። በመደበኛ ፍርድ ቤት መጽደቅ አለበት። (ሰ/መ/ቁ 240810)

​3. ስጦታ ይርጋ :- ባል ወይም ሚስት ያለ ሌላኛው ፈቃድ የጋራ ንብረት በስጦታ ሲሰጥ፣ ይህን ውል የመሻር የይርጋ ጊዜ (Statute of Limitations) የቤተሰብ ሕጉ ሁለት ዓመት ሳይሆን፣ የፍትሐብሔር ሕግ የተመለከተው የአስር ዓመት ጊዜ ነው። (ሰ/መ/ቁ 247605)

ምንጭ:- Aberham Yohanes

Comments

Be the first to add a comment