ስለባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ስለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር አዲሱ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 ምን እንደሚል ቀጥሎ በአራት ክፍል የምናይ ይሆናል፡፡
መልካም ምንባብ!
ክፍል አንድ፡- ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (One person private limited Company)፣
ስለ ማህበሩ ባህሪያት እና አመሠራረት
ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማለት አንድ ሰው በግሉ በሚሰጠው መግለጫ (Unilateral Declaration) መሠረት የተቋቋመ የንግድ ማህበር ነው:: ማህበሩ ከአባላት የተለየና የተነጠለ የራሱ የህግ ሰውነት ወይም corporate existence አለው፡፡ ይህን ማህበር ለማቋቋም የሚያስፈልገው አነስተኛ ካፒታል መጠን ብር 15,000 (አስራ አምስት ሺህ) ነው፡፡
ይህ የንግድ ማህበር በአገራችን ከተለመዱት የንግድ ማህበራት የተለየ ሲሆን በአዲሱ የንግድ ህግ የተካተተበት ምክንያት አንድ ማህበር (ኩባንያ) ለመመስረት በቂ ካፒታል የያዘ ባለሃብት የግድ ምናባዊ (fictitious) ማህበርተኛ መፈለግ እንዳይገደድ ፤ የተለያየ ካፒታል በመመደብ ለሥራ የሚውለውን ገንዘብ ነጥለው ሥራ መስራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች እድል ማመቻቸት፤ በሌሎች ሃገራት የተለመዱ የንግድ ማህበራት ወደ ሃገራች ማካተት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚመሠረተው አባሉ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ፅ/ቤት በመቅረብ በሚሠጠው መግለጫ መሰረት ነው፡፡ ይህን መግለጫ መመስረቻ ፅሁፍን የተካ ነው፡፡ መግለጫው ማህበሩ ከተለመዱት ዝርዝሮች በተጨማሪ አንድ አባል ብቻ ያለው መሆኑን፣አባሉ የሞተ፣ የጠፋ ወይም በፍርድ የተከለከለ እንደሆነ ስለ ወራሾች ወይም ስለአባሉ ሆኖ ሕጋዊ ተግባራትን እዲፈፅም የታጨው የንብረት ጠባቂ ሰው ስም እና ዕጩ ንብረት ጠባቂው ፍቃደኛ ሆኖ ኃላፊነቱን የተቀበለ መሆኑ ሊያካትት ይገባል፡፡
ዕጩ ንብረት ጠባቂ መሰየም የምስረታ ቅድመ ሁኔታ በመሆኑ ዕጩ ንብረት ጠባቂው ዕጩነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ፅ/ቤት ቀርቦ ካላረጋገጠ ማህበሩ ሊመሰረት አይችልም፡፡ አንድ ንብረት ጠባቂ በአንድ ጊዜ ለተለያዩ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለሆኑ ማህበራት ንብረት ጠባቂ ሆኖ ሊሾም አይችልም፡፡
አንድ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሌላ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሊያቋቋም አይችልም ይህን ተላላፎ የተቋቋም ማህበር ያገባኛል በሚል ሰው ጠያቂነት ሊፈር እንዲሁም በምስረታው ምክንያት እና በኋላ ለሶስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት አባሉና ማህበሩ በአንድነትና በተናጠል ኃላፊ ይሆናሉ፡፡
አንድ ግለሰብ ነጋዴ (Sole proprietor) ወደ ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማህበር መለወጥ የሚችል ሲሆን ግለሰቡ ማህበሩን ከመመስረቱ በፊት ለገባበት ዕዳ ሁሉ ከማህበሩ ጋር በአንድነትና በተናጠል ኃላፊ ይሆናል፡፡
ኦምኒኤል (12/02/2014 ዓ.ም)

Comments

Be the first to add a comment