የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ሰላም ይብዛለዎት!!
ሰሞኑን ለወራት ተቋርጦ የነበረው ከመሬት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች እንደገና መጀመሩን ሁላችንም ሰምተናል፡፡
ታዲያ ከሚጠየቁት አገልግሎቶች አንዱ የሰነድአልባ መስተንግዶ በመሆኑ በዚች መልእክት ከመመሪያ 17/2006 በክፍል 2 ባለመብቶች ሊያሟሉ ስለሚገባቸው መስፈርቶችና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ስለሚጠበቅባቸው ሀላፊነት የሚከተለውን ያንብቡልኝ!!!
እስከ ግንቦት 1988 ዓ.ም ድረስ ለተያዙ ይዞታዎች ባለይዞታነትን ለመወሰን መሟላት ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችና መረጃዎች፡-
በቅድሚያ ይዞታው ላይ ከግንቦት 1988 ዓ.ም በፊት የሰፈረ ቤት ወይም ቤትና አጥር መኖሩ ከሶፍራቶፕ ወይም ከኖርቴክ (የአየር ካርታ) ወይም ከጂአይኤስ መረጃ ላይ ይጣራል፡፡
ቤቱ በሶፍራቶፕ ወይም በኖርቴክ (የአየር ካርታ) ወይም በጂአይኤስ መረጃ ላይ የማይታይ ቢሆንም ስለቤቱ መንግስታዊ በሆነ ተቋም ከግንቦት 1988ዓ.ም በፊት የተሰጠ ሰነድ ማቅረብ እና ቤቱ ከ1988 ዓ.ም በፊት ተገንብቶ በእጃቸው የሚገኝ መሆኑ በወረዳው አስተዳደር ተረጋግጦ ከቀረበ፣
ቤቱ የግለሰብ ስለመሆኑ ግልፅ መረጃ ባልተገኘባቸው ይዞታዎች ቤቱና ይዞታው ወይም ቤቱ የመንግስት አለመሆኑ፡-ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በሚገኝ መረጃ ማለትም ከመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ፣ ከወረዳው ወይም ከክ/ከተማው የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ወይም ከቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት በደብዳቤ በመጠየቅ ይረጋገጣል፤
የተጠቀሰውን መረጃ የተጠየቁት ተቋማት በ30 ቀናት ውስጥ የተጠየቁትን መረጃ ካልሰጡ በተገኘው መረጃ ባለይዞታውን ግዴታ በማስገባት እንዲስተናገድ ይደረጋል፤ ለተቋማቱም ምላሽ በወቅቱ ባለመስጠታቸዉ በህዝብና በመንግስት ጥቅም ላይ ለሚፈጠር ችግር ኃላፊነቱን እራሳቸዉ የሚወስዱ መሆኑ ተገልጾ ከመጀመሪያዉ መረጃዉ ሲጠየቅ በደብዳቤ እንዲያዉቁት መደረግ አለበት፡፡ ካርታው ከመታተሙ በፊት ተቃዋሚ ካለ በፍ/ቤት በማሳገድ ወይም የመንግስትና የህዝብ ንብረት መሆኑን የሚገልጹ ማስረጃዎችን በመያዝ ለክ/ከተማው ፕሮጀክት ጽ/ቤት በ30 ቀን ጊዜ ውስጥ እንዲያቀርብ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ እንዲታወጅ ይደረጋል፡፡
በሲአይኤስ መረጃ ላይ በማን ስም እንደተመዘገበ ይታያል፤ ሆኖም በሲአይኤስ መረጃ ላይ ያለው መረጃና ከእነዚህ ተቋማት በሚገኘው መረጃ መካከል ልዩነት ከተፈጠረ በዚህ መመሪያ ላይ ስለመረጃ እርማት በተቀመጠው አግባብ ታይቶ ይወሰናል፡፡
በዚህ መመሪያ ላይ በተደነገገው መሰረት ይዞታውና ቤቱ የማን እንደሆነ ይዞታው ከሚገኝበት ወረዳ በአሁኑ ጊዜ ይዞታው በመስተንግዶ ጠያቂዉ ወይም በሕጋዊ ወኪሉ እጅ ስለመኖሩ ወይም እያስተዳደረው ስለመሆኑ በወረዳው አስተዳደር ተጣርቶና ተረጋግጦ የሚቀርበው መረጃ ተቀባይነት ያለዉ ሆኖ፣ በደጋፊ ሰነድነት፣
ቦታውን ያገኙበት ማስረጃ ማለትም የቀድሞ ካርታ፣ ደብተር፣ ወራሽ ከሆኑ የወራሽነት ማስረጃ፣ በግዥ ወይም በስጦታ ያገኙ ከሆኑ የዉል ሰነድ፣ ከአዋጅ 47/67 ዉጭ በመወረሳቸዉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪና የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ለባለመብቶቹ የተመለሱ ቤቶችና ይዞታዎች ከሆኑ በኤጀንሲዉ የተረጋገጠ የዉሳኔ ሰነድ እና ከተመሳሳይ ማስረጃዎች መካከል ቢያንስ አንዱን ወይም፣ የቦታ ኪራይና የቤት ግብር ማሳወቂያ /ቢል/፣ የመሰረተ ልማት አገልግሎት (የውሃ/የመብራት/የስልክ) ያስቀጠሉበትን ሰነድ፣ የቤት ግብርና የቦታ ኪራይ የከፈሉበት ሰነድ እና ሌሎች ሕጋዊ የሰነድ ማስረጃዎች ካሉ ተቀባይነት የሚኖራቸዉ ይሆናል፡፡
በከተማው ፕላን ወይም የአካባቢ ልማት ፕላን አንጻር ተቃርኖ የሌለባቸው ይዞታዎች ብቻ መስተንግዶ የሚሰጥ ሲሆን የፕላን ተቃርኖ ያለባቸው ይዞታዎች ለህዝብ ጥቅም ሲባል በሚለቀቅ መሬት ላይ ለሰፈረ ንብረት ስለሚከፈል ካሳና ምትክ ቦታ አሰጣጥ የአፈጻጸም መመሪያ በተገለጸው መሰረት ይዞታው እንዲለቀቅ ይደረጋል፡፡
የተዘረዘሩት እንደተጠበቁ ሆኖ በመስክ መረጃ ሲሰበሰብ የድንበር ክርክርና የይገባኛል ጥያቄ ካልቀረበበት መስተንግዶ ይሰጣል፡፡
በነገረዎት ላይ ከዚህ በታች ያሉት በተለያየ ዘመን ከመሬት ጋር በተያያዘ ለመለኪያነት ሲያገለግሉ የነበሩ በመሆናቸውና በጽሁፉም በተደጋጋሚ ሲጠቀሱ ስለነበር ከነአገልግሎት ዘመናቸው ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ እንደሚከተለው ተቀምጠዋል፡፡
"የሶፍራቶፕ ማፕ" ማለት እስከ 1964 ዓ.ም የነበሩ ይዞታዎችን አካቶ ቤት ለቤት በተደረገ የቅየሳ ስራ ተደግፎ የተዘጋጀ ማፕ ነው፡፡
"የኖርቴክ ማፕ" ማለት በ1986 ዓ.ም ከአየር በረራ በተነሳ ፎቶ ወደ ዲጅታል ማፕ የተቀየረ መረጃ ነው፤
"የጂ.አይ.ኤስ መረጃ" ማለት እስከ ግንቦት 1988 ዓ.ም ድረስ የተያዙ ይዞታዎችን ቤት ለቤት በተደረገ የቅየሳ ስራ እና የኖርቴክ ማፕ ጋር በማዋሀድ የተዘጋጀ መረጃ ነው፤
"የካዳስተር መረጃ" ማለት እስከ ግንቦት 1988 ዓ.ም ድረስ የነበሩ ይዞታዎችን በቤት ለቤት የይዞታ ልኬት፤ የህንጻ/ቤት የግንባታ ቁሳቁሶች እና ሶሽዮ ኢኮኖሚክ መረጃዎችን አሰባስቦ የያዘ መረጃ ነው፡፡
መብተዎትን ባለመግዛት ለሕግ የበላይነት የድርሻዎትን ይወጡ!!!
ሲሳይ ሰማኝ
የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም
Comments
Be the first to add a comment