ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት

መግቢያ
ጉዳይን ያለ አግባብ ማጓተት በተገልጋዩ ህብረተሰብ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ባለ ግንኙነት የሚፈጸም ተገቢነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ተገልጋዩ የህብረተሰብ አባል በህግ ክርክሮች እና በአስተዳደር አከላት የሚሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ለማግኘት ወደተለያዩ መንግስታዊ አና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ፊት ይቀርባል፡፡ በዚሁ ሁኔታ አገልግሎት ፈልጎ የቀረበው ተገልጋይ እንደ ጉዳዩ ባህሪ በህግ እና አሰራር በተቀመጠ ምክንያታዊ ጊዜ ውስጥ ለጉዳዩ እልባት አግኝቶ መሸኘት አለበት፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ተገልጋዮችን ተገቢ ላልሆነ እንግልት በመዳረግ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን እንዲያባክኑ በማድረግ ለከፋ ምሬት እና ተስፋ መቁረጥ በመዳረግ በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻክር ይሆናል፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍም ጉዳይን አለአግባብ ማጓተት ምንነት እና የሚያስከትለውን የህግ ተጠያቂነት በአጭሩ የምንዳስስ ይሆናል፡፡

ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት ምንነት
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ህገመንግስት አንቀጽ 12 ላይ የመንግስት ስራ በግልጽነት እና ተጠያቂነት በሰፈነበት ሁኔታ መከናወን እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ይህ መርህ በህግ እና አስተዳደራዊ ውሳኔዎች አሰጣጥ ላይ ተፈጻሚነት አለው። የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቋቋሙበትን አላማ ለማሳካት የሚያስችሏቸው የገልግት መስጫ ስታንዳርድን የሚያመለክቱ የተለያዩ መመሪያዎች እና የአሰራር ስርአት አላቸው፡። ከነዚህ መካከልም ጉዳዮችን ተቀብለው ውሳኔ የሚሰጡበትን የጊዜ ገደብ የሚያመላክቱ ድንጋጌዎች በአዋጅ በደንብ እና መመሪያዎች የተደነገጉ ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም በዜጎች ቻርተር፣ በመሰረታዊ የአሰራር ለውጥ(ቢፒአር) እና ሌሎች የለውጥ መሳሪያዎች እንደየ ጉዳዮቹ ባህሪ እና የውስብስብነት ደረጃ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አንድን ጉዳይ ተቀብለው መርምረው እልባት የሚሰጡበትን የጊዜ ገደብ ያመላክታሉ፡፡ እነዚህን በህግ የተዘረጉትን የአሰራር ደረጃ ባለመጠበቅ ጉዳይን ያለ በቂ ምክንያት ሳይወስኑ ወይም ሳይፈጽሙ ማቆየት ጉዳይን ያለአግባብ የማጓተት ትግባር ነው፡፡

በፍትህ አስተዳደር ዘርፍ ያለውን በምናይበት ጊዜ በመርህ ደረጃ የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ የሚቆጠር ነው፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 20 (1) መሰረት ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ክስ ከቀረበበት በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ የመሰማት መብት እንዳለው ተደንግጎ ይገኛል፡፡

በዚህም ጉዳያቸው ታይቶ የመጨረሻ ፍርድ ያልተሰጣቸውን ተከሳሾች በተገቢው ጊዜ ፍርድ መስጠት የሚገባ ሲሆን ውሳኔ አስከሚያገኙ በእስር የሚቆዩበትን ጊዜ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ፍርድ እንደተሰጠ ተደርጎ ሊታይ አይገባውም፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንኡስ ንቀጽ 3 መሰረት ማንኛውም በወንጀል ፍርድ ሂደት ውስጥ ያለ ሰው ከጥፋተኝነት ፍርድ በፊት በተከሰሰበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ሊቆጠር እና ሊታይ አይገባውም፡፡ በወንጀል ጉዳይ የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት የተከሰሱ ሰዎች መብት ብቻ ሳይሆን ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችም መብት ነው፡፡ በዚህም በህገመንግስቱ አንቀጽ 19(3) መሰረት በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰአት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው ለመታሰር ያበቃቸውን በቂ ምክንያት የማወቅ መብት አላቸው፡፡ ለመታሰራቸው በቂ ምክንያት የሌለ ከሆነ ፍ/ቤቱ የኣካል ነጻነታቸውን ጠብቆ በነጻነት ሊለቃቸው እንደሚገባ ነገር ግን ልዩ በሆነ ሁኔታ ፍትህ እንዳይጓደል ምርመራ ለማካሄድ አስፈላጊ የሆነውን ተጨማሪ የእስር ማቆያ ጊዜ በጥብቅ መስፈርት ሊፈቅድ ይችላል፡፡

ከዚህም የምንረዳው በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙም ሆነ የተከሰሱ ሰዎች በህገመንግስቱ በተጠበቀላቸው መብት መሰረት ጉዳያቸው ሳይጓተት ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ በፍትሐብሄር ፍትህ አስተዳደርም ፍርድ ቤቶቻችን የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች እንደ ጉዳዩ ውስብስበነት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ አይቶ አከራክሮ ለመወሰን የሚያስችላቸው የፍትሀብሄር ስነስርአት ህግ እና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 008/2013 ጉዳይን በተወሰነለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ያለማጓተት መወሰን እንደሚገባ አመላካች የአሰራር ስርአቶች ናቸው፡፡

ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት በወንጀል እና በፍትሐብሄር ጉዳይ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በማናቸውም አስተዳደራዊ ጉዳዮችም ጭምር ተቀባይነት የሌለው የአሰራር ብልሹነት ነው፡፡ የፌደራል አስተዳደር ስነ ስርአት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አንቀጽ 33 ላይ “በተገቢው ጊዜ መወሰን” በሚል ርእስ እንደተደነገገው የአስተዳደር ውሳኔ የሚሰጠዉ ሰዉ የአስተዳደር ውሳኔዉን ሳይዘገይ በተገቢዉ ጊዜ መስጠት እና በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ጥቅሞች በውሳኔው መዘግየት ምክንያት ለጉዳት እንዳይጋለጡ ማድረግ አለበት በማለት በመደንገግ በግልጽ ጉዳይን ያለ አግባብ ማጓተት ህገወጥ እንደሆነ የደነገገ ሲሆን ከውጤት አንጻርም የአስተዳደር ውሳኔው በተገቢው ጊዜ ሳይሰጥ መቅረት የአስተዳደር ውሳኔ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ እንደተሰጠ ውሳኔ ይቆጠራል በማለት አስቀምጦ ይገኛል፡፡ በአገራችን የህግ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ይሄው የአስተዳደር ስነ ስርአት አዋጅ የአስተዳደር አካላት የተገልጋዮችን መብት በማክበር ጉዳያቸውን ሳያጓትቱ በተገቢው ፍጥነት መወሰን እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡ በዚሁ አግባብ አለመወሰንምጥያቄውን ውድቅ እንደማድረግ ይወሰዳል፡፡ ይህ ማለትም ተገልጋዩ ወደሚከተለው አቤቱታ ሰሚ የበላይ የመንግስት አካል ቅሬታውን ማቅረብ እና ምላሽ ማግኘት ይችላል ማለት ነው፡፡

ጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት
ለጉዳይን ያለአግባብ ማጓተት ወንጀል ተጋላጭ የሆኑት የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ህዝባዊ የሆኑ የግሉ ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንም የሚያካትት ነው፡፡ ከዚሁ አኳያ በተገልጋዮች ላይ የሚፈጸም ምክንያታዊ ያልሆነ የጉዳይ ማጓታት ተግባር ከአስተዳደራዊ እና የፍሐብሄር ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን በወንጀልም የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 18 መሰረት ማንኛውም የመንግስት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ በሃላፊነቱ በስራው ምክንያት በቀረበለት ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲል በጉዳዩ ላይ ጥቅም ያለውን ማንኛውንም ሰው ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት በማሰብ ከህግ፣ ከመመሪያ ወይም ከተለመደው አሰራር ውጪ ያለበቂ ምክንያት ጉዳዩን ያልወሰነ፣ ያዘገየ ወይም ባለጉዳይን ያጉላላ ሰው እንደ ጉዳዩ ሁኔታ በመቀጮ ወይም በቀላል እስራት ወይም ከአምስት አመት በማይበልጥ ጽኑ ሰእስራት እና አመስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ደንግጎ ይገኛል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው በአዋጁ እንደተደነገገው ጉዳይን ማጓተት ወንጀል የሙስና ወንጀል የሆነበትን መሰረታዊ ምክንያት ነው፡፡ በዚሁም መሰረት የሙስና ወንጀሎች በመሰረታዊነት የሚፈጸሙት የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለአንዱ ወገን በተለያዩ ምክንያቶች በማዳላት ሌላውን ወገን ለመጥቀም በማሰብ ነው። የዚህ ወንጀል ፈጻሚዎች ጉዳይን አለአግባብ የማጓተት ተግባር የሚፈጽሙት ባለጉዳዩ በመመላለስ ምክንያት ከሚደርስበት እንግልት ለማምለጥ ሲል ገንዘብ እንዲከፍላቸው ተጽእኖ ለማሳደር አለያም ባለጉዳዩ ተማሮ ጉዳዩን መከታተሉን እንዲተወው በማድረግ የባለጉዳዩን መብት ለመረጡት ሌላኛው ሰው በማስተላለፍ በዚህም የሚከፈላቸውን ተገቢ ያልሆነ

Comments

Be the first to add a comment