የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
ሰላም!
መቼም ሁሉም ሰው ሻጭም ገዥም ነው ሲባል ሳይሰሙ አልቀሩም። አባባሉ እውነት አለው። ለምን ቢሉ! እዚህ መንደር ሻጭ ሆኖ የምናውቀው ሰው በሌላ ጊዜና ቦታ ገዥ ወይም ሸማች ሆኖ ይገኛልና ነው። አስረጅ አምጡ ከተባለም የሰፈርዎን ባለሱቅ ዋቢ አድርገን እናቀርባለን። እርሱ በእርስዎ ሰፈር አለ የተባለ ነጋዴ ይሁን እንጂ መርካቶ ወይም አትክልት ተራ ላለ ነጋዴ አለ የተባለ ሸማች ወይም ገዥ መሆኑን ልብ ይሏል!
እናም ከስር የሰፈሩትን የሸማቾች መብቶች ራስዎን እንደሸማችም እንደነጋዴም እያዩ እንዲያነቧቸው እንጋብዝዎታለን።
ማንኛውም ሸማች፦
1. ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና አይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት አለው፤
2. ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት መብት አለው፤
3. የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ መብት አለው፤
4. በማንኛውም ነጋዴ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድ እንዲሁም በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ መብት አለው፤
5. በገዛው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ላይ ያገኛቸውን ጉድለቶችና ጉድለቶቹ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ጉዳት ለሚመለከተው የመንግስት አካል የማሳወቅ መብት አለው፤
6. ጉድለት ያለበት የንግድ ዕቃ የተሸጠለት ወይም ጉድለት ያለበት አገልግሎት የተሰጠው ከሆነ ግዥው በተፈፀመ በ15 ቀናት ውስጥ የንግድ ዕቃው እንዲለወጥለት ወይም አገልግሎቱ በድጋሜ ያለክፍያ እንዲሰጠው ወይም የከፈለው ብር እንዲመለስለት ሻጩን የመጠየቅ መብት አለው፤
7. የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት የንግድ ዕቃዎቹን ወይም አገልግሎቶቹን በማቅረብ የተሳተፉ ነጋዴዎች በተናጠል ወይም በአንድነት ካሳ እንዲከፍሉት የመጠየቅ መብት አለው።
ከንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 የተወሰደ
ፋሲካ አጌና (አቃቤ-ህግ)
ግንቦት 1 ቀን 2014 ኣ.ም
Comments
Be the first to add a comment