የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
የመከላከል መብት
• የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት
የተከሰሱ ሰዎች በህገ መንግስቱ ከተከበረላቸው ሰብዓዊ መብቶች መካከል “የመከላከል መብት” አንዱ መሆኑን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀጽ 20/4/ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሰረት የተከሰሱ ሰዎች “የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡” ስለዚህ የመከላከል መብት ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ ያገኘ መብት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
ይህን “የመከላከል መብት” በተመለከተ ፍ/ቤቶች ያላቸው ሚና ሲታይ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 13/1/ መሰረት “የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ አለባቸው” ከዚህ አኳያ ፍ/ቤት የተከሰሱ ሰዎች የመከላከል መብታቸውን በሚገባ መጠቀም እንዲችሉ አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት በሕግ አግባብ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል እንጂ በምንም መልኩ ይህን መብት ለሚገድብ ድርጊት አስተዋጽኦ ማድረግ የለበትም፡፡ ፍ/ቤት የተቀላጠፍ ፍትህ አሰጣጥን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተከሰሰው ሰው ምስክሮቹን ለማቅረብ ያለው አቅም እና የተመቻቸ ሁኔታ፣ በማረሚያ ቤት መሆኑን እና አለመሆኑን፣ የመከላከያ ማስረጃና ምስክሮችን ለማቅረብ የሚጠይቀውን እገዛ፣ በቂ ነው ሊባል የሚችል ጊዜ እና አጠቃላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ መብት ተጠቃሚ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ ፍ/ቤት ይህን ሕገ መንግስታዊ ሃላፊነትና ግዴታውን በአግባቡ መወጣት አለበት፡፡
ሰ/መ/ቁ. 100860 ቅጽ 18፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀጽ 20/4/፣ 13/1/
በወንጀል ጉዳይ የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማንኛውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸው ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት እንዳላቸው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 20(4) ተደንግጎ የሚገኝ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህንን ሕገ መንግስታዊ መብት ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት ደግሞ ክስ የቀረበባቸው መሆኑን በወ/መ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 123 በተመለከተው መሰረት በሚላክ መጥሪያ እንዲያውቁት ሲደረግ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 94227 ቅጽ 16፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 20(4)
ምንጭ
የኢ/ ፌ/ዴ/ሪ/ሕገ መንግስት
የኢ/ፌ/ዴ/ሪ/ወንጀል ሕግ
mr zee
Comments
Be the first to add a comment