👉 በ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ 19 ሺህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

▪️ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ ተገንብተው የተጠናቀቁ የገበያ ማዕከላትን እና የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክቶችን መርቀዋል።

▪️በ2017 በጀት ዓመት በመዲናዋ 19 ሺህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ከንቲባዋ አንስተዋል።

▪️በመዲናዋ የገበያ ማዕከላትን እና የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን በማስፋት የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

▪️ከሜክሲኮ እስከ ለገሃር 13 የሚሆኑ የመኪና ፓርኪንጎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል ነው ያሉት። በአንድ ጊዜ ብቻ ከ2 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም እንዳላቸውም ገልጸዋል።

⏺በተጨማሪም አስር ተርሚናሎች ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህም በአንድ ጊዜ ብቻ  ከ1 ሺህ 600 በላይ ተሽከርካሪዎችን እንደሚይዝ ተናግረዋል።

▪️ከአሁን በፊት በከተማዋ በቂ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች ባለመኖራቸው ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ችግር እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ አሁን ላይ የተገነቡት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክቶች የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ  ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

▪️በመዲናዋ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑት የገበያ ማዕከላት መካከል የስኬት እና የአፍሪካ ኅብረት የገበያ ማዕከላት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የገበያ ማዕከላት የከተማውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት እና የተለያዩ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ በማቅረብ እንድሁም የሥራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የገለጹት።

▪️የአካባቢውን ማኅበረሰብ አቅም ባገናዘበ ሁኔታ ምርትን ከማቅረብ በተጨማሪ ምቹ የግብይት ምኅዳር እንዲኖር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

▪️ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት ፕሮጀክቶች የካፍቴሪያ፣ የመዝናኛ፣ የሱቅ አገልግሎት፣ የመፀዳጃ ቤቶች፣ ዘመኑን የዋጁ የደኅንነት ካሜራዎች እና ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን ያሟሉ ናቸው።

💫በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳዩ እና ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጡ ስለመሆናቸውም ተጠቁሟል።

@etconp

Comments

Be the first to add a comment