ቸር ይግጠመን
በቦሌ ክ/ከ/ዐ/ጽ/ቤት የህ/ም/መ/ዳይሬክቶሬት የቴልግራምመልክት የተዘጋጀ ነሐሴ 7/12/2013
በሰላም ይገላገሉ
ውድ የቴሌግራም ተከታታዮቻችን ማንም ሰው ለአቅመ አዳም /ሄዋን/ ደርሶ ስራ ከያዘ፣ ቀጥሎ ማሳካት ከሚፈልጋቸው ነገሮች አንዱ መውለድ ወይም ዘሩን መተካት ነው፡፡
መውለድ ደግሞ የግል ብቻ ሳይሆን ለሀገር ቀጣይ ተረካቢ ትውልድ የማፍራት ጉዳይ ስላለበት መንግስታትም ለሰራተኞቻቸው ከሚሰጧቸው መብቶች አንዱ የወሊድ ፈቃድ በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010የወሊድ ፈቃድ በሚል የሚከተለውን ደንግጓል እንደሚከተለው አቅርበነዋልና ለመውለድ ከምታደርጉት ዝግጅት አንዱ ይህንን ማንበብ ይሆን ዘንድ እጋብዛለሁ፡፡
አንቀጽ 42 የወሊድ ፈቃድ
1.ነፍሰጡር የሆነች የመንግስት ሰራተኛ፣
ሀ. ከእርግዝናዋ ጋር የተያያዘ ምርመራ ለማድረግ ሐኪም በሚያዘው መሰረት ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣታል፣
ለ. ከመውለዷ በፊት እረፍት እንድታደርግ ሐኪም ካዘዘ ደመወዝ የሚከፈልበት እረፍት ይሰጣታል
2.በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1)የተመለከተው ፈቃድ እንደ ህምም ፈቃድ አይቆጠርም
3.ነፍሰጡር የሆነች የመንግስት ሰራተኛ መውለጃዋ ሲደርስ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችበት ቀን በፊት 30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ፣ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90 ተከታታይ ቀናት፣ በአጠቃላይ 120 ተከታታይ ቀናት ደመወዝ የሚከፈልበት የወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል
4.በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (3) መሰረት ሰራተኛዋ የተሰጣት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከማለቁ በፊት ከወለደች ያልተጠቀመችበትን ቀሪ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወለደች በኋላ እንድትጠቀምበት ይደረጋል
5.ሰራተኛዋ የወሰደችው የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ሲያልቅ ያልወሰደችው የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ሲያልቅ ያልወለደች እንደሆነ እስከምትወልድበት ቀን ድረስ ባሉት የስራ ቀናት የምትቆይበት እረፍት በበጀት ዓመቱ ካላት የዓመት ፈቃድ የሌላት እንደሆነ ከሚቀጥለው የበጀት ዓመት የእረፍት ፈቃዷ ይተካል
6.ሰራተኛዋ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (3) የተወሰነውን የወሊድ ፈቃድ ከጨረሰች በኋላ ብትታመምና ተጨማሪ ፈቃድ የሚያስፈልጋት መሆኑ በሐኪም ከተረጋገጠ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 43(1) በተደነገገው መሰረት የሕመም ፈቃድ መውሰድ ትችላለች
7.ማንኛውም ስድስት ወር የሞላት ነፍሰጡር የሆነች የመንግስት ሰራተኛ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከመውሰዷ በፊት ጽንሱ የተቋረጠባት ከሆነ ይህንኑ የሚያረጋግጥ የህክምና ማስረጃ ስታቀርብ የ60 ቀን የድህረ ወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል
8.የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወሰደች በኋላ የጽንስ መቋረጥ ካጋጠማት የወሰደችው የቅድመ ወሊድ ፈቃዷ ተቋርጦ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (3) የተመለከተው የ90 ቀን የድህረ ወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል
9.ከሶስት እስከ ስድስት ወር ባለው የእርግዝና ጊዜ ውስጥ የፅንስ መቋረጥ ያጋጠማት የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ የሚከፈልበት 30 ተከታታይ ቀን ፈቃድ ይሰጣታል
10.ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ የትዳር ጓደኛው ስትወልድ ደመወዝ የሚከፈልበት 10 የስራ ቀን ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡
በነገራችን ላይ ከዚህ በፊት የነበረውን አዋጅ ስድስትን በአዋጅ ሀምሳስድስት መቀየር ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል፡-
የጽንስ መቋረጥ ላጋጠማቸው ሴቶች የሚሰጠው ፈቃድ፤
የወሊድ ፈቃድን ከ90 ቅድመ ወሊዱን ጨምሮ ወደ 120 ቀናት ያሳደገው፤
እንዲሁም በክፍል 5 አንቀጽ 48/6 የተደነገገው ማንኛውም መስሪያቤት ህጻናት ማቆያ ማቋቋም እንዳለበት የሚደነግጉት ናቸው፡፡

አዘጋጅ ሲሳይ ሰማኝ

Comments

Be the first to add a comment