👉በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለሚመሰረቱ ከተሞች ማስተር ፕላን የማዘጋጀት ሥራ መጀመሩ ተገለጸ

💫በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለሚመሰረቱ ከተሞች ማስተር ፕላን የማዘጋጀት እንዲሁም የአሶሳ ከተማን የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ፤ 'ሲቲስ አሊያንስ' በተሰኘ ድርጅት አማካኝነት በይፋ መጀመሩን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ አስታውቋል።

ፕሮጀክቱን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እና ሲቲስ አሊያንስ በጋራ ተግባራዊ እንደሚያደርጉት የክልሉ የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ደርበው ዘንቶ ለአሐዱ ተናግረዋል።

"ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ አምስት ከተሞች ላይ የሚከናወን ነው" ያሉም ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ ከተማ አሶሳ እና በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚመሰረት ከተማ መመረጡን አስታውቀዋል።

በዚህ መሠረት "ለአሶሳ ከተማ ለ30 ዓመታት የሚያገለግል የማስፋፊያ ፕላን እና በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ለሚመሰረቱ ከተሞች ደግሞ አዲስ ፕላን የማዘጋጀት ሥራ በይፋ ተጀምሯል" ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ እንደ ክልል ለጊዜው "አበንኮሮ" የተሰኘ አንድ ከተማ ብቻ ተመስርቶ ማዘጋጃ ቤት መቋቋሙንም ገልጸዋል፡፡

የሚመሰረቱት ከተሞች የቱሪዝም ከተሞች እንደሚሆኑ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ከተማው ዓለም አቀፍ ሆቴሎች እና ሪዞርቶችን እንደሚያካትት ገልጸዋል።

ወደፊት በአካባቢው ብዙ ከተሞች ይመሰርታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹም ሲሆን፤ አካባቢው የዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን ትኩረት መሳቡን ጠቁመዋል።

ቀደም ሲልም የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ አልሚዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የሐይቁን መሃል በተመለከተ ከፌደራል መንግሥት ጋር በትኩረት የሚሰራ መሆኑ የተጠበቀ ቢሆንም ብዙ ደሴቶች በመኖራቸው ጥናት እንደሚፈልግ ለአሐዱ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የአሶሳ ከተማ ከሦስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ ማስተማር ፕላኑ ተሰርቶ ሥራ ላይ መዋሉን ጠቁመዋል።

"ነገር ግን ከተማዋ ከሕዳሴው ግድብ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን በፍጥነት እያደገች ነው" ብለዋል።

ሆኖም ለ30 ዓመታት የሚያገለግል የማስፋፊያ ፕላን በማስፈለጉ በሲቲስ አሊያንስ ድርጅት አማካኝነት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

Via አሐዱ ሬዲዮ

@etconp

Comments

Be the first to add a comment