የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ

ውድ አንባቢያን በያላችሁበት ሰላም እንድትሆኑ የዘወትር ምኞታችን ነው፡፡
በዛሬው መልዕክት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን አስፈጻሚ አካላት እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ 74/2014 ከተቋቋሙት ቢሮዎች አንዱ ስለሆነውና በተለይም ከዚህ ቀደም በሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ስር የነበሩ ተግባራትን ወደዚህ ቢሮ የተዛወሩ በመሆኑ እንግልትን ለመቀነስ ይረዳል በሚል ከዚህ እንደሚከተለው አቅርቢያለሁ!!፡፡
በአሰሪና ሠራተኛ መካከል የሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል፤ የወል የሥራ ክርክሮች እና የኅብረት ስምምነት ድርድር ልዩነቶች በመግባባት እልባት እንዲያገኙ ያደርጋል፤ የህብረት ስምምነቶችንና ማሻሻያቸውን ይመዘግባል፤
በአሰሪና ሠራተኛ መካከል የሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን የትምህርትና የሥልጠና አገልግሎት ይሰጣል፣ የሙያ ምክር አገልግሎት ስለሚስፋፋበት፣ ክፍት የሥራ መደቦች ስለሚመዘገቡበትና ሥራና ሠራተኛ ስለሚገናኙበት ዘዴ ይቀይሳል፤ ሲጸድቅም ተግባራዊ መሆኑን ያረጋግጣል፤
አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር በከተማው ውስጥ በሥራ ላይ ስለተሰማራውና ሥራ አጥ ስለሆነው የሰው ኃይል፣ ስለሙያ መደብ፣ የከተማውን የስራ ሰምሪት እንዲሁም የሙያ አመዳደብ ጥናትና ምርምር ያደርጋል፤ መረጃዎችን ይይዛል፤ የስራ ገበያ መረጃዎች ስርዓት ይዘረጋል፣ ይሰበስባል፣ ያጠናክራል፤ ያሰራጫል፤
በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ህግ በተደነገገው መሰረት በከተማው ውስጥ የሚደራጁ የአሰሪና ሰራተኛ የሙያ ማህበራትን ይመዘግባል፤ ድጋፍ ይሰጣል፤ ሲፈርሱ ምዝገባውን ይሰርዛል፤
አሰሪዎች የስራ ሁኔታን፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነትንና የስራ አካባቢን ለመጠበቅ የወጡ የስራ ሁኔታ ደረጃዎችና የመከላከያ ዘዴዎች በሥራ ላይ ማዋላቸውን ይቆጣጠራል፤
ሥራና ሠራተኛ ለሚያገናኙ ኤጀንሲዎች የብቃት ማረጋገጫ በህግ መሰረት ይሰጣል፤ ድጋፍ ያደርጋል፤ መሥራታቸውን ያረጋግጣል፤ ይሰርዛል፤
በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ህግ መሰረት የከተማው አስተዳደር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ያቋቁማል፤ የቦርዱን አባላት ይሰይማል፤ ያሰናብታል፤ ተግባርና ኃላፊነታቸውን ይከታተላል፤
የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን፣ የሥራ ሥምሪት አግልግሎትና የሥራ አፈጻጸም እያጠና ምክር የሚሰጠው የመንግሥት፣ የአሠሪዎች ማህበራትና የሠራተኛ ማህበራት ተወካዮችን ያካተተ ቋሚ የሆነ አማካሪ ቦርድ ሊያቋቁም ይችላል፤
የከተማ ነዋሪው ስለውጭ አገር ሥራ ስምሪት እና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጨባጭ ሁኔታ፤ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝ የመገናኛ ብዙኃንንና ሌሎች አማራጭ ዘዴዎችን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ከተማ አቀፍ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን ያከናውናል፤
ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ስለተቀባይ አገር ሁኔታ በሚሰማሩበት የስራ መስክ ሊኖራቸው ስለሚገባ ክህሎት፣ ስለመብታቸውና ኃላፊነታቸው እና ስለመሳሰሉት ጉዳዩች የቅድመ-ስምሪትና የቅድመ ጉዞ ግንዛቤ ማሰደጊያ ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል፤
ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም "ሥራ" ማለት አግባብ ባለው ሕግ የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የስራ ገበያ መረጃ፣ የሙያ ደህንነት ጤንነትና የሥራ አካባቢ፣ የሠራተኛና የአሰሪዎች ማህበር፣ ማህበራዊ ምክክር ሥርዓት፣ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ እና መሠረታዊ የሥራ ላይ መብቶችና ግዴታዎችን አካትቶ የያዘ ነው፡፡

ሲሳይ ሰማኝ
ቸርይግጠመን!!!

Comments

Be the first to add a comment