👉የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአዳማ - አዋሽ የፈጣን መንገድ ሁለተኛው ክፍል፣ የመልካጂሎ - አዋሽ፣ ሎት 2 ፈጣን መንገድ ከ181 ሚሊዮን ዶላር በላይ ፋይናንስ ሊያደርግ ነው

በአፍሪካ ልማት ፈንድ የፋይናንስ ድጋፍ ለማካሄድ ግምገማና ውይይት ሲደረግበት የነበረው የአዳማ - አዋሽ የፈጣን መንገድ ሁለተኛው ክፍል፣ የመልካጂሎ - አዋሽ፣ ሎት 2  የፋይናንስ ድጋፍ ድርድር በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር  መካከል የመጨረሻ የፋይናንስ ድርድር ተካሄደ።
ይህ ድርድር ባንኩ ፕሮጀክቱን ለማጸደቅ በቅርቡ ለባንኩ ቦርድ ከማቅረቡ በፊት የጋራ ግንዛቤ እና ስምምነት ለማድረግ እንዲያስችል የተደረገ ነው።

የዚህ ፕሮጀክት አላማ በዋናነት የፍጥነት መንገድ መገንባት እንዲሁም ተጓዳኝ መሰረተ ልማቶችን ማሻሻል ያካትታል።

የፍጥነት መንገድ ግንባታው በሁለት (2) ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን፣ የመጀመሪው 48 ኪ.ሜ በአፍሪካ ልማት ፈንድ ፋይናንስ የሚደረግ ሲሆን፣ ቀሪው 19 ኪ.ሜ በኮሪያ ኤግዚም ባንክ እንደሚሸፈን ይጠበቃል፡፡

ፕሮጀክቱ በዋናነት የሚያካትታቸው የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ የቴክኒክ ድጋፍ አገልግሎቶች፣ የሎጂስቲክስ፣ የትራንስፖርትና የንግድ፣ ተቋማዊ ድጋፍና አቅም ግንባታ፣ ለአካባቢው ህብረተሰብ የሚሠሩ ተጓዳኝ የልማት ሥራዎች፣ የካሳ ክፍያ እና የመልሶ ማቋቋም ይገኙበታል፡፡

ይህ መንገድ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳንን የሚያካትት ሁለገብ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የትራንስፖርት ትስስር ለማሻሻል ታሳቢ ያደረገ ነው።

የዚህ ኮሪደር ፕሮጀክት አላማ ቀልጣፋ እና ውጤታማ የትራንስፖርት ስርዓት እንዲኖር ማድረግ፣ የንግድ እና በአካባቢው ያሉ አገራትን እርስ በእርስ ማስተሳሰር ነው።

ፕሮጀክቱ ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ለድህነት ቅነሳ ጥረቶች እና በፕሮጀክቱ አካባቢ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን በማነቃቃት ድህነትን ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያደርጋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል 138.66 ሚሊዮን UA ወይም ባለው ወቅታዊ ምንዛሪ 181.5 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ ለማድረግ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን፣ መንግስትም እስከ 26.12 ሚሊዮን UA (34.2 ሚሊዮን ዶላር) ፋይናንስ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል በድርድሩ ውጤት መሰረት ፕሮጀክቱን ለባንኩ ቦርድ አቅርቦ በማጸደቅ፣ በቀጣይ የፋይናንስ ስምምነት በመፈራም እ.ኤ.አ በ2026 መጀመሪያ ላይ ወደ ትግበራ መግባት ነው።

በሌላ በኩል ቀጣዩን 19 ኪሜ የሚሆነውን የመንገድ ክፍል በተመለከተ ከኮሪያ ኤግዚም ባንክ ጋር የሚደረጉ ንግግሮች ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ይጠቁማል።

@etconp

Comments

Be the first to add a comment