~ተስፋ ካለ አሁንም ሕይወት አለ‼️

• ይህች ያለንባት ሀገረ ዱንያ የተፈጠረችበትን ባህሪዋን ብቻ ነው የምታሳየን፡፡ እኛው በክስተቶቿ እንደመማለን እንታመማለን እንጅ ዱኒያ ከባህሪዋ ውጭ የሆነን አዲስ ነገር ይዛ አልመጣችም፡፡ ዱኒያ ጀነት አይደለችምና አላህ ቀድሞውኑ ይህችን አገር ሲፈጥራት የፈተና፣ የመከራ፣ የበሽታ፣  የስደት፣ የልዩ ልዩና በርካታ መሰናክሎችና ውጣ ውረዶች ዓለም አድርጎ ነው ። ዱንያ የዕድሜ ጥፍጥናዋ በሞት የመረረ፣ ጤናዋ በበሽታ የተበረዘ፣ ደስታዋ በሀዘን ብዛት የደፈረሰ፣ ሰላሟ በጦርነት የተናጋ፣ ምቾቷ ከችግር ያልተላቀቀ፣ ስኬቷ ከውድቀት ጋር የተዳቀለ፣ ችግሯ እልፍ ቀዳዳዋ ሺህ የሆነች ሀገር ናት።
አኑራ የምትገድል፣ አስቃ የምታስለቅስ፣ ሰጥታ የምትነሳ፣  አክብራ የምታዋርድ፣  አገናኝታ የምታለያይ ናት። ዱንያ ትልቁን ስታሳንስ፣ ያመናትን ስትከዳ ግድየላትም፡፡ የሰራላትን ስትገፋ ይሉኝታ የሚባል ነገር አይዛትም፡፡

• ደረጃው ይበላለጥ እንጅ ወደ መሬቷ ውስጥ የገባም ሆነ በላይዋ ላይ የሚኖር ሁሉ ከችግሮቿ ዓይነቶች ቢያንስ በአንዱ ተገርፏል። ሁሉም በፈተናዋ ጉድ አይቷል፤ ከሙሲባዋ« ኡ ኡ ! ገላግሉኝ»ብሏል ። ዱኒያ አልነካህም ብላ ቃል የገባችለት ማንም ሰው የለም። አዎ የለም፡፡

• ታዲያ የዱኒያን ተለዋዋጭ ገፅታ በጥልቀት ያየና  በአትኩሮትም ያስተዋለ ሰው በደረሰበት የዱኒያ ላይ ሙሲባ ምክንያት አይደነግጥም፡፡ ለፈተና መከራዋም እጅ አይሰጥም፡፡ ፈጣሪዉንም አያማርርም።በሚሠራው ሁሉ አላማ ያለውና ምክኒያታዊ የሆነው ጌታችን አላህ ፍርዱም ሆነ ሥራው አድሎ የሌለበት ነዉና በሚሰራው አይጠየቅም፤በሚፈርደውም ቅሬታ አይቀርብበትም። ከሱ በላይ ፍርዱ ያማረ ለባሮቹ  አዛኝ የለምና፤ በደረሱብን ሙሲባዎች ሁሉ ነገራችንን ሁሉ ለሱ ትተን ክፍፍሉን መውደድና ምርጫውን መቀበል ይገባናል። የደረሰብን ሙሲባ የቱን ያህል ቢከፋና ህመሙ ዘልቆ ቢሰማንም እንኳ አላህን ከሚያስደሰት ቃል ውጭ መናገር የለብንም፤ ከሙእሚን ባህሪም መውጣት አይገባንም።

• ማን ያውቃል አዎን ማን ያውቃል! እኛ መጥፎ ሆኖ የታየን መልካም፤ መልካም ሆኖ የታሰበን ደግሞ መጥፎ ሊሆን ይችላል።
ማን ያውቃል ! አላህ የከለከለን እኮ ሊሰጠን፤ የጣለን ሊያነሳን፤ ያዘገየን በሰላም ሊያደርሰን፤ ያላመቻቸልን ቆይቶ ሊሸልመን፤ ያላሣካልንና ሊያሻሽለን ይሆን ይሆናል።አንድ የአላህ ባሪያ ፈጣሪውን ምንጊዜም በጥሩ ነገር ያስባል ይጠረጥራል፤ ፈጣሪውም መልካሙን ጥርጣሬውን ያፀናለታል። ሙእሚን ምንጊዜም ቢሆን ተስፋ አይቆርጥም፡፡አንድ ቀን ያሰብኩት ይሆንልኛል ብሎ ተስፋ ያደርጋል … ብደሀይ ያልፍልኛል፣ ብወድቅ ይሳካልኛል፣ ባጣ ይተካልኛል፣ ጌታዩ አላህ ሁሉንም ያደረገው ለኔው መልካምን ሽቶ የኔንም መሻሻል ፈልጎ ነው ሲል ያስባል፡፡

• ሙእሚን እንደ ስሙ ሁሉ በአላህ ከልቡ አማኝ ነዉና በደረሰበት ትንሽ የዱኒያ ላይ ጊዜያዊ ሙሲባ ተቆጥቶ ዛሬውኑ ቂያማ ትቁም አይልም፡፡ ተቆጥቶም እራሱንም ሆነ ሰውን አይረብሽም፡፡ ለንዴቱ ማብረጃም ገመድ ፍለጋ አይሮጥም፡፡ የህይወትን ባህሪ ያውቃል ስለሚያውቅም ይረጋጋል፡፡ አምላኩን ፈጣሪዉን አላህ ስለሚወድ ከሱ የሚመጣዉን ሁሉ ይወዳል፡፡ ለዚህም ችግርን እንደ ደስታ በሽታን እንደ ሀጢአት ማበሻ አድርጎ ይመለከታ። አብሽሩ ሕይዎት ይቀጥላል…!

©AbuSufiyan

🌱 @TewhedandSuna

1 comment

🥀فأين تذه‍بون
Ensha allah🥺