" የሪል ስቴት አልሚዎች ገንብተው የማያስረክቡትን ቤት ከገበያ ዋጋ በታች በመሸጥ ላይ ይገኛሉ " - ማኅበሩ

በኢትዮጵያ የሪል ስቴት ኢንዱስትሪው የሕዝብ አመኔታ በማጣቱ ምክንያት እየተቀዛቀዘና እየሞተ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበር አስታወቀ።

የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዓለማየሁ ከተማ ፥ " የሪል ስቴት ኢንዱስትሪው የሕዝብ አመኔታን በማጣቱ እንዳያድግና ወደፊት እንዳይራመድ እየሆነ ይገኛል " ማለታቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

የሪል ስቴት አልሚዎች ለቤት ፈላጊዎች በውላቸው መሠረት ቤቶቻቸውን ገንብተው ባለማስረከባቸውና ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው ዘርፉን በሕዝብ ዘንድ አመኔታ እንዳይኖረው አድርጎታል።

አቶ ዓለማየሁ፣ " የሪል ስቴት አልሚዎች ገንብተው የማያስረክቡትን ቤት ከገበያ ዋጋ በታች በመሸጥ ላይ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ በርካታ ገንዘብ ከሕዝብ በመሰብሰብ ለክስና ውዝግብ መነሻ እየሆነ ይገኛል " ብለዋል።

አክለውም አልሚው ለቤት ፈላጊው ማኅበረሰብ ታማኝ ሆኖ ቤት ማስረከብ ባለመቻሉ ዘርፉ እየተቀዛቀዘና እየሞተ ይገኛል ሲሉ አስታውቀዋል።

" ታማኝ ሆኖ በገባው ውሉ መሠረት ቤት ገንብቶ የማያስረክብ ሪል ስቴት አልሚ እና ወረቱን የሚበላ ነገዴ አንድ ናቸው "  ያሉ ሲሆን ማኅበራቸው በቤት አልሚዎችና ገዥዎች መካከል መተማመን እንዲኖር የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ማኅበሩ ከተመሠረተ የአንድ ዓመት ጊዜ ቢኖረውም ከዋጋ በታች በውሸት ማስታወቂያ ገዥው እንዳይጭበረበርና ዘርፉ በሕግ እንዲመራ የማድረግ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

" በኢትዮጵያ የሚገኝ ማንኛውም ሪል ስቴት አልሚ ፈቃድ አግኝቶ በሕጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ አሠራር ተዘርግቷል፤ ችግር ተፈጥሮ ከተገኘም ፈቃዱ የሚነጠቅበትና የሚጠየቅበት ሥርዓትም ተበጅቷል " ብለዋል።

ይህ መረጃ ከሪፖርተር ጋዜጣ የተገኘ ነው።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሚያዚያ 1 ቀን 2018 ዓ/ም

@tikvahethiopia

1 comment

Abdulqehar Tassew
አዎ እንዴት ይታመኑ, ለምሳሌ ጎጆ ብሪጅ የሚባል ብሬን ሰልቅጦ የለም, አቶ ፍስሃ 1.2ሚለየን ብሬን ይዞ አሜሪካ ገባ ከዚህ በላይ ለቀሩት መዋጮ አይደለም ህዝብ ገንዘብ ሚያድለው, እረ ተውን መንግስት እራሱ ጉዳዩን በህግ ይይዝና አመላልሶ አመላልሶ የታክሲ የነዳጅ አስወጥቶን ጊዜያችን አቃጥሎ ውጤት ወፍ....በቁስልህ ላይ እንጨት ስደድን ተውት